ኮርፖሬሽኑ 250 የፀረ ተባይ ኬሚካል መርጫዎች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ 250 የፀረ ተባይ ኬሚካል መርጫዎች ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የአንበጣ መከላከል ስራውን የሚያግዝ 250 የፀረ ተባይ ኬሚካል መርጫ ድጋፍ አደረገ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራአስፈፃሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ድጋፉን ለግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን አስረክበዋል።
ዋና ስራአስፈፃሚው የፀረ-ተባይ መርጫው ኮርፖሬሽኑ በጎርፍና በአንበጣ ለጠፉ ማሳዎች ምትክ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያና ለማሳ ዝግጅት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ የተደረገ ነው ብለዋል።
የኮርፖሬሽኑ ድጋፍ ቀጣይ እንደሆነም ገልፀዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴንም በኮርፖሬሽኑ የተደረገው ድጋፍ ችግሩ ሳይሰፋ ለመከላከል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የፀረ-ተባይ መርጫው በሰው ኃይል ርጭት ለማካሄድ እንደሚያግዝና ሌሎች ተቋማትም ባላቸው አቅምና ሃብት አንበጣውን ለመከላከል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በሚኒስቴሩ የተቋቋመ ኮሚቴ የሚደረገውን ድጋፍ ተቀብሎ ወደ ክልሎች በማሰራጨት ስራ ላይ እንዲውል እያደረገ መሆኑንም አቶ ዑመር ገልፀዋል።
የቻይና መንግስት ኢትዮጵያ አንበጣውን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ትናንት ሁለት ተሽከርካሪዎች፣ 58 ሺህ 400 ሊትር ጸረ-ተባይ ኬሚካል፣ ሁለት ሺህ በእጅ የሚያዙ የኬሚካል መርጫዎች፣ 20 ሺህ የግል ደህንነት መጠበቂያ አልባሳት፣ የአፍና ፊት መሸፈኛ ጭምብሎችና ጓንቶች ድጋፍ ማደረጉ ይታወቃል።