አንበጣ በታየባቸው አካባቢዎች 600 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቁጥጥር ስራ ተከናውኗል... ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
አንበጣ በታየባቸው አካባቢዎች 600 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቁጥጥር ስራ ተከናውኗል... ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ጥቅምት 10/2013 (ኢዜአ) አንበጣ ከታየበት 800 ሺህ ሄክታር መሬት በ600 ሺህ ሄክታሩ ላይ የቁጥጥር ስራ መካሄዱን ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሰብላቸውን አንበጣ ያጠፋባቸው አርሶና አርብቶ አደሮች ወደፊት በምግብ ዋስትና መርሃግብር ይደገፋሉም ተብሏል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ለኢዜአ እንዳሉት በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው አንበጣ እስካሁን በምርት ላይ ስላደረሰው ጉዳት የተካሄደ ጥናት ባይኖርም በመሬት ስፋት ምን ያህል ሽፋን እንዳለው መግለጽ ይቻላል።
እንደ ዶክተር ማንደፍሮ ገለፃ በ2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ጥናት ተካሂዶ በ800 ሺህ ሄክታር ላይ አንበጣ ታይቷል።
አንበጣ በታየበት ቦታ ሁሉ ጉዳት ላያደርስ ይችላል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው እንደ ግለሰብ ያረፈበትን ማሳ ሊያጠፋ ቢችልም እንደ አገር ያደረሰው ጉዳት በማክሮ ደረጃ አልታየም ብለዋል።
ቅኝቱን ተከትሎ በሰው ኃይል፣ በአውሮፕላንና በተሽከርካሪ ላይ በሚገጠም መሳሪያ የኬሚካል ርጭት ሲደረግ መቆየቱንም ገልፀዋል።
በርጭቱ ወቅት አውሮፕላኖች በመከስከሳቸውና ለሞተር እድሳት በመሄዳቸው ችግር መፈጠሩንም አስታውሰዋል።
ይሁንና አንበጣው የሚያደርሰውን ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ በሰው ኃይል ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ በስምንት አውሮፕላኖችና ከ120 በላይ በሆኑ ተሽከርካሪዎች የኬሚካል ርጭቱ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
አንበጣ በታየበት 600 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተካሄደው የቁጥጥር ስራም በሰብል ላይ ያደርስ የነበረውን ጉዳት መቀነስ ያስቻለና የኢኮኖሚ ፋይዳውም የላቀ እንደሆነ ተናግረዋል።
አንበጣው ሙሉ በሙሉ ማሳቸውን ያጠፋባቸው አርሶና አርብቶ አደሮች በቀጣይ በምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ታቅፈው ድጋፍ እንዲያገኙ እንደሚደረግም ዶክተር ማንደፍሮ ገልፀዋል።
በአካባቢያቸው የውሃ አማራጭ ያላቸውም በቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን ዘርተው እንዲያመርቱ እንደሚደረግም እንዲሁ።
የምርምር ተቋማትን የትንበያ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው በየዓመቱ እንደሚከሰቱት ሌሎች ተባዮች ለአንበጣም ትኩረት ያሻዋል ሲሉ ነው ያሳሰቡት።
የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢሴሞ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በመደበኛ ተባዮች ላይ የምርምር ስራዎች ሲሰራ ቢቆይም አንበጣ ላይ እስካሁን የተሰራ ምርምር አለመኖሩን ተናግረዋል።
አሁን አንበጣ እያደረሰ ያለውን ጉዳትና ፀባዩን የሚያጠኑ ሁለት ቡድኖች ተዋቅረው አንበጣ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎቸ መላካቸውን ገልፀዋል።
በቡድኖቹ ውስጥ የሚገኙት ተመራማሪዎች ናሙና በመውሰድ ምርምር አካሂደው እስከቀጣዩ ሣምንት የደረሱበትን ውጤት እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል ብለዋል።