ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴን ለመገንባት በቂ ምክንያት አላት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴን ለመገንባት በቂ ምክንያት አላት
አዲስ አበባ ጥቅምት 10/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴን ለመገንባት በቂ ምክንያት አላት ተባለ።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንደማንኛውም ድንበር ተሻጋሪ የወንዞች ልማት ውዝግቦችን ቢያስነሳም ግድቡ ለአካባቢያዊ ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ዕድል እንደሚሰጥ በሰሜን ካሎሪና ዩኒቨርሲቲ የዊልሰን ዓለማቀፍ ማዕከል አባል የሆኑትና በሰላምና መረጋጋት ላይ የሚጽፉት አሮን ሳልዝበርግ ይገልጻሉ ።
ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት የሚያስችል በቂ ምክንያት እንዳላትና ከጠቅላላ ህዝቧም 45 በመቶ ብቻ የሚሆኑት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሶ የሚገነባው ግድብ በሀገሪቱ ጠቅላላ ኢኮኖሚ ዕድገትና በድህነት ቅነሳ ስራው ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጸሀፊው የጠቀሰው።
የግድቡ መገንባት ግብጽ ባለፉት ጊዚያት ፖለቲካዊ ጫና በማድረግ የአባይ ወንዝን ኢ-ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ለልማቷ ስትጠቀምበት የነበረውን አካሄድ ለማስተካከል አንድ መንገድ ሆኖ ያገለግላል ያሉ ሲሆን፤ ግድቡ የውሃ አጠቃቀምን ብቻ ሳይሆን የቀጠናውን የሀይል ሚዛን በማመጣጠን ሚዛናዊ አካሄድንም ሊያንጸባርቅ እንደሚችል ጸሀፊው አክለው ገልጸዋል።
የውሃ ሀብት ፍትሃዊና ዘላቂ ተጠቃሚነትን በተመለከተ ከአካባቢው ዜጎች በበለጠ የውጭ አደራዳሪዎች የችግሩን ቀጠናዊም ሆነ አካባቢያዊ ፈተና በቀላሉ ሊረዱት አይችሉም ያሉት ጸሀፊው።
በመሆኑም የሚደረጉ ድርድሮች የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሀገራት በራሳቸው ተነሳሽነት ማካሄድ ቢችሉ መልካም መሆኑን ገልጸዋል።
የአደራዳሪዎች መኖር ግድ ከሆነ እንኳን ሚናቸው መሆን ያለበት ሀሳብና መረጃዎችን መስጠት፣አጀንዳዎችን ማስተካከል እና በመሰል ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሞክሮ ማጋራት ላይ ብቻ የሚወሰን መሆን ይገባዋል ሲሉ ጸሀፊው ገልጸዋል።
ሁለቱ ሀገራት በአባይ ወንዝ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የጋራ ጉዳዮቻቸውም ዙሪያ የጋራ ትብብር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ማጠናከር የሚችሉ ከሆነ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን የልማት፣ የዕድገት፣ የሰላምና የደህንነት ምልክት ማድረግ እንደሚችሉም ጸሀፊው ገልጸዋል።