ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የከተማዋ ትምህርት ቤቶች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10/2013(ኢዜአ) በአዲስ አበባ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በመከላከል ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን የከተማዋ ትምህርት ቤቶች ገለጹ።

በከተማዋ በያዝነው ወር ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት ታቅዷል።

የከተማዋ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን  ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተገሩት የቫይረሱን ስርጭት በመከላከል የመማር ማስተማር ሂደት ለማስጀመር ጥረት እያደረጉ ነው።

በትምህርት ቤቶቹ የመማሪያ ክፍሎች የኬሚካል ርጭት እየተደረገባቸው ነው።

የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች ፣ ሳሙና፣ ሳኒታይዘርና የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የመማር ማስተማር ሂደት በፈረቃ እንደሚሆንና በአንድ ክፍል 25 ተማሪዎች ርቀታቸውን ጠብቀው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ አስታውቀዋል።

ለዚህም ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችና ወንበሮች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

የሐምሌ 1967 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ወይዘሪት ሀለውያ ሁሴን እንደሚሉት ከምዝገባ ጀምሮ ተማሪዎች ርቀታቸውን ጠብቀው የሚስተናገዱበት አሰራር ተቀምጧል።

መምህራንም ርቀታቸውን ጠብቀው የመማር ማስተማር ተግባራቸውን እንደሚያከናውኑ ይደረጋል።

የሙቀት መጠኑ ከፍ ያለ ተማሪ ቢገኝ፤ ለብቻው ቆይታ የሚያደርግበት ቦታ መዘጋጀቱንም ርዕሰ መምህርቷ አስታውቀዋል።

የብርሃነ ሕሊና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ወይዘሮ አበባዬ ደምሴ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ከወረርሽኙ ራሱን ጠብቆ የመማር ማስተማር ሥራውን እንዲጀምር እየተሰራ ነው።

የበላይ ዘለቀ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ዳንኤል አመንቴ በበኩላቸው ተማሪዎችን ከስጋት ነፃ በሆነ መልክ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየሰራ ነው።

በአሁኑ ወቅት መምህራን የቫይረሱን ስርጭት አስመልክተው በየቀኑ መደበኛ ትምህርት ከመጀመራቸው አስቀድመው ለተማሪዎቻቸው ግንዛቤ  ይሰጣሉ ብለዋል።

የተማሪ ፖሊሶችን በማደራጀት እያንዳንዱ ተማሪ ራሱን ከወረርሽኙ እንዲጠብቁ ቁጥጥር እንደሚደረግ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ 26 ሚሊዮን ተማሪዎች ባለፉት ሰባት ወራት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በመደበኛ መልኩ ያልተከታተሉ ቢሆንም፤ ቤታቸው ሆነው በቴክኖሎጂ በታገዘ ትምህርት ለመስጠት ጥረት ተደርጓል።

ኮቪድ-19 ባሳደረው ተጽዕኖ በዓለም 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን የሚደርሱ ተማሪዎች ለበርካታ ወራት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም