በድሬዳዋ አስተዳደር ገጠርና ከተማ ትምህርት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ አስተዳደር ገጠርና ከተማ ትምህርት ተጀመረ

ድሬዳዋ፣ ጥቅምት 9/2013 (ኢዜአ) በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የመማር ማስተማር ስራ ዛሬ በድሬዳዋ አስተዳደር ገጠርና ከተማ ተጀመረ።
በአስተዳደሩ ሳቢያን በሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በገጠርና የግል ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር ሂደቱን ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የካቢኔ አባላት ናቸው፡፡
የመማር ማስተማሩ ሂደቱን ተዘዋውረው የተመለከቱት የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አህመድ መሀመድ ተማሪዎች የኮሮና ወረርሽኝ በመከላከል ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስትር የተዘጋጀውን የትምህርት ማስጀመሪያ መስፈርት በማሟላት የተጀመረው ትምህርት ስኬታማ እንዲሆን አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
በመማር ማስተማር ሂደት የክፍል እጥረት ለሚያጋጥማቸው ትምህርት ቤቶች አስተዳደሩ ህንፃዎችን ይከራያል ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሀመድ በበኩላቸው የመማር ማስተማሩ ስራ እንደ ትምህርት ቤቶች ተጨባጭ ሁኔታ በፈረቃ ለማስቀጠል በ150 ትምህርት ቤቶች መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ለትምህርት ቤቶች የወንበር፣ ጠረጴዛ፣ ሰሌዳና መሰል ግብአቶች ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ መሟላቱን አመልክተዋል፡፡
ዛሬ በከተማ የስምንተኛ እና 12ተኛ ክፍል ተማሪዎች የክለሳና ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ በገጠር ትምህርት መጀመሩንም አስረድተዋል፡፡
በሚቀጥለው ሣምንት በአስተዳደሩ የሚገኙ 104 ሺህ ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ትምህርታቸውን ይጀምራሉ ብለዋል፡፡
የመምህራን እጥረትን ለመፍታት ከእሳቸው ጀምሮ የካቢኔ አባላት፣ በጎ ፍቃደኞች፣ በጡረታ የተገለሉ መምህራን የዜግነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡
በየትምህርት ቤቱ የእጅ መታጠቢያ ፣ሳኒታይዘር፣ ከፌደራል መንግስት የተለገሰ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ለተማሪዎች መሰራጨቱንም ጠቅሰዋል፡፡
የጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ ተማሪዎች ራሳቸውን ከኮሮና በመጠበቅ ለሀገር፣ ቤተሰብና ማህበረሰብ ጤና የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የተዘጋጀው የጤና አጠባበቅ ፕሮቶኮል በየትምህርት ቤቱ መተግበሩን ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡
የሣቢያን ቁጥር አንድ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር መስፍን አበጋዝ መምህራን የተጀመረው ትምህርት በስኬት እንዲጠናቀቅ ሌት ተቀን ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
“ትምህርት ቤቱ እስከ ቅዳሜ በአራት ፈረቃ የመማር ማስተማሩን ሥራ ዛሬ ጀምሯል” ብለዋል፡፡
የውሃ እጥረትን ለመፍታት ልዩ ትኩረት ለገጠር ትምህርት ቤቶች መሰጠት አለበት ያሉት ደግሞ የለገ ቢራ ገጠር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት አልፊያ መሀመድ ናቸው፡፡
የስምንተኛ ክፍል ተማሪ አቤል ፍሬው በሰጠው አስተያየት "ትምህርት በመጀመሩ ደስተኛ ነኝ ፤ ራሳችንን ከኮሮና የመጠበቅ ኃላፊነታችንን በመወጣት ዛሬ የጀመርነውን ትምህርት በስኬት ለማጠናቀቅ ተዘጋጅተናል ብሏል፡፡