የብር ኖት ለውጥ ፋይዳዎች - ኢዜአ አማርኛ
የብር ኖት ለውጥ ፋይዳዎች

በመንግስቱ ዘውዴ (ኢዜአ)
በአገራችን የወረቀት የብር ኖት ለመገበያያነት ስራ ላይ የዋለው ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መግቢያ ጀምሮ መሆኑን የተለያዩ ሰነዶች ያመለክታሉ። ይህን ተከትሎም በተለያዩ ጊዜያት ለተለያየ ዓላማ የብር ኖት ለውጦች ተካሂደዋል። ወደ አምሳ ዓመት በተጠጋው የአፄ ሃይለስላሴ የንግስና ዘመን ለአራት ጊዜያት ያህል የብር ኖቶች ለውጥ ስለመደረጉ ይነገራል። ከዚያ ቀጥሎም በደርግ ዘመነ መንግስት፣ በኢህአዴግና አሁን አገሪቱን በሚመራው የብልጽግና ፓርቲ የብር ኖቶች ተቀይረዋል።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የዘውዳዊን መንግስት በሚገልጽ መልኩ ሲያሳትሙ፣ የደርግ መንግሥት ደግሞ የዘውዳዊውን ሥርዓት ካበቃ በኋላ በ1969 ዓ.ም የንጉሡ ምስልን የያዙትን የመገበያያ ገንዘቦች ለውጥ በማድረግ የብር ኖት ቅያሬ አድርጓል።
በተመሳሳይም ኢህአዴግ ደርግን አሸንፎ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ለሰባት ዓመታት ያህል ቀድሞ የነበረውን ገንዘብ ሲጠቀም ቆይቶ በ1990 ዓ.ም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የድንበር ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ በደርግ ዘመን ከታተመው ብር ላይ መጠነኛ ማሻሻያ በማድረግ ለውጥ አድርጓል። ይህ የገንዘብ ኖት እስከ መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ስራ ላይ የዋለ ሲሆን 23 ዓመታትን አገበያይቷል።
በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም ነባሮቹን የብር ኖቶች (አምስት ብርን ሳይጨምር) ሙሉ በሙሉ በአዲስ በመተካትና ለመጀመሪያ ጊዜ ባለ200 የብር ኖት በማካተት ስራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል። መንግሥት አሮጌ የብር ኖቶቹን ለመቀየር የሦስት ወር የጊዜ ገደብ አስቀምጧል። በአገሪቱ ታሪክ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ አገልግሎት ላይ የነበሩት የገንዘብ ኖቶች ባለ1፣ 5፣ 10፣ 50 እና 100 ብር ኖቶች ሲሆኑ ለረጅም ጊዜ ከፍተኛ ዋጋ ያለው የገንዘብ ኖት 100 ብር ሆኖ ቆይቷል። ስለሆነም አሁን ወደ ገበያ እንዲገባ የተደረገው የባለ 200 ብር ኖት በታሪክ ሁለተኛው ከፍተኛ ዋጋ ያለው የብር ኖት ሆኗል።
በአገሪቱ የተካሄዱት የብር ኖት ለውጦች ዓላማና ምክንያቱ እንደየወቅቱ የመንግስት አስተዳደር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ የተለያየ እንደመሆኑ መጠን በቅርቡ የተደረገው የገንዘብ ለውጥም የራሱ የሆነ ዓላማ እንዳለው መንግስት ይፋ አድርጓል።
የብሔራዊ ባንክ ለዚሁ ጉዳይ ማስፈጸሚያ ባዘጋጀው መመሪያ ላይ እንዳመለከተው የአሁኑ የብር ኖት ለውጥ ዋነኛው ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ነው። በአገሪቱ ከባንክ ውጭ የሚንቀሳቀስ በቢሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ በመኖሩ ወደ ባንክ ስርዓት ለማስገባት፣ ሙስናንና ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር እንዲሁም ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ለማተም የሚደረጉ ሕገ ወጥ ጥረቶችን ለማስቀረት ያለመ መሆኑን ተነግሯል።
በተለይ በአገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች መደረግ ከጀመሩባቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እንደሚካሄድ በተደጋጋሚ በሚወጡ ሪፖርቶች በመረጋገጡ ይህንን ለመከላከል የብር ኖት ለውጥ ማድረግ ማስፈለጉም ተነግሯል። በእነዚህ ዓመታት በህገወጥ መንገድ ታትሞ በአገሪቱ የተሰራጨ ገንዘብ መኖሩንና ይህም ለኢኮኖሚ ግሽበቱ ዋነኛ መንስኤ በመሆኑ ይህን ለመቆጣጠር ታሳቢ የተደረገ ስለመሆኑም መንግስት አሳውቋል።
የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዢው ዶ/ር ይናገር ደሴ የብር ኖት ለውጥ የተደረገበትን ምክንያት ሲያብራሩ “አብዛኛው ኅብረተሰባችን ግብይት የሚያደርገው ከባንክ ውጭ ነው። በዚህ ምክንያት ብዙ ጥሬ ገንዘብ ከባንክ ውጭ ይገኛል። በዚህም የጥሬ ገንዘብ እጥረት ባንኮች ላይ የማጋጠም እድሉ ሰፊ ነው። በመሆኑም ይህ የብር ኖት ለውጥ ለገቢ አሰባሰብ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል የሚል እምነት አለን፤ ለአጠቃቀምም የተሻለ አገልግሎት ይሰጣል" ብለዋል።
በአንድ አገር በተለያዩ ምክንያቶች ገንዘብ ከባንክ ይልቅ በግለሰቦች እጅ ሊከማች እና በግለሰቦች እጅ የሚገኘው ገንዘብ ሲበዛ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ መልኩ በሚደርስ ተጽዕኖ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆልን ለመታደግ ደግሞ በግለሰቦች እጅ የተከማቸውን ገንዘብ ለመሰብሰብና ወደ ባንክ እንዲገባ ለማድረግ የገንዘብ ኖት መቀየር የግድ አስፈላጊ እንደሚሆንም የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።
የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት የገንዘብ ኖት ለውጥ ማድረጓ ብዙ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት ይገልጻሉ። በተለይ ከባንክ ውጭ ያለው ገንዘብ ወደ መደበኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ ሂደት ለማምጣት እንደሚረዳ ይናገራሉ።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ “the Ethiopian Economist View” በሚለው የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ የብር ኖት ለውጡ ከባንኮች ውጭ የሚንቀሳቀሰውን ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብ ወደ መደበኛ የፋይናንስ ሥርዓቱ ለማስገባት፣ የባንኮችን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ፣ የቁጠባ መጠን ለማሳደግና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ አቶ አዲሱ እጥፉ ይህንኑ ሃሳብ በማጠናከር ሂደቱን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግና ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር በመመሪያ መደገፍ እንዳለበት ይናገራሉ።
ከኢዜአ ጋር በዚሁ ዙሪያ ቆይታ ያደረጉት በመቱ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት መምህር አቶ ናትናኤል አብረሃም የብር ኖት ለውጡ ህገወጥ የገንዘብ ዝውወርን በማስቀረትና የባንኮችን የካፒታል አቅም በማጠናከር ኢንቨስትመንቱን የሚያፋጥነው ስለመሆኑ ነው የሚያገልጹት።
በተመሳሳይ የዩኒቨርስቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋከልቲ ዲን አቶ እንዳለ ዓለሙ የብር ኖት ለውጡ በአገሪቱ ጤናማ የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንዲኖር ያደርጋል ይላሉ። መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ከባንክ ስርዓት ውጪ በህገወጥ መንገድ መንቀሳቀሱ ኢኮኖሚውን ከመጉዳቱ ባለፈ የህብረተሰቡን ሰላም፣ ጤናና ማህበራዊ ህይወት ለመጉዳት አስተዋጽኦ አለው የሚሉት ደግሞ በዩኒቨርስቲው የቢዝነስ ማኔጅመንት ክፍል ኃላፊ አቶ ሱሌይማን አብደላ ናቸው።
እንደ ባለሙያዎቹ ትንታኔ በአገሪቱ ከባንክ ሥርዓት ውጭ የሚንቀሳቀስ ከፍተኛ ገንዘብ በመኖሩ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲዛባ አድርጓል። ለዚህም በማሳያነት የሚጠቅሱት የብሔራዊ ባንክ ካሳተመው ብር በላይ በህገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ታትሞ ገበያ ውስጥ መሰራጨቱን የሚያመለክቱ ጥናቶች በተለያዩ ጊዜያት ይፋ ስለመሆናቸው ነው።
ይህ ህገ ወጥ የገንዘብ ስርጭት የዋጋ ግሽበትን በመፍጠር በገበያ ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲከሰት አድርጓል። የዋጋ ጭማሪ ከተከሰተ ኢንቨስትመንት አዋጭ አይሆንም፣ ኢንቨስትመንት ከሌለ ደግሞ የግለሰቦች ገቢ ይቀንሳል፤ በዚህ ምክንያት አጠቃላይ አገራዊ ኢኮኖሚው እንዲቀንስ ያደርጋል።
በሌላ መልኩ ደግሞ በሙስና የተዘረፈ ከፍተኛ ብር ካለ ባንክ ከመውሰድ ይልቅ በቤት ማስቀመጥን ስለሚመርጡ የገንዘብ እጥረት እንዲከሰት በማድረግ የመንግስት የገንዘብ ስርዓት እንዲዛባ ያደርጋል። በዚህ ምክንያት ባንኮች ለኢንቨስተሮች እንደልባቸው ገንዘብ ማበደር እንደማይችሉና መንግስት ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ እንደሚቸገር ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
የኢትዮዽያ ባንኮች ማህበር ሪፖርት እንደሚጠቁመው ከአምስት ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ2016 ከባንክ ውጭ ሲዘዋወር የነበረው 63 ቢሊዮን ብር በከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ በማሳየት እ.አ.አ በ2020 ከ113 ቢሊየን ብር በላይ ደርሷል።
ይህም በሀገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅር ላይ ጉልህ ችግር ሊፈጥር የሚችል በመሆኑ በመንግስት ሊወሰዱ ይገባል ያላቸውን የማስተካከያ እርምጃዎችን አቅርቦ እንደነበር ማህበሩ አመልክቷል። በምክረ ሃሳብ ከቀረቡት መካከል መንግስት ከባንክ ውጪ ያለ ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ ወደ ባንክ ስርዓት እንዲገባ ማድረግ፣ ከባንክ ውጪ በግለሰብ እጅ ላይ ሊቀመጡ የሚችለው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ጣሪያ እንዲወስን፤ የብር ኖት ቅያሬ በማድረግ ኢኮኖሚውን እንዲደግፍ ማድረግ እንደሚገባና የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ያላቸውን አማራጮች አቅርቦ ነበር።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር እንደሚገልጸው የብር ኖቶች በአዲስ መተካታቸው የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ አስተዋጽኦ አላቸው። ከአጭር ጊዜ አንጻር በባንኮች ከፍተኛ የገንዘብ ክምችት እንዲኖር ያደርጋል፤ ቁጠባም ያበረታታል። ሀሰተኛ የገንዘብ ዝውውርን ከማስወገዱም በተጨማሪ በጥቁር ገበያ ያለውን የህገ-ወጥ ምንዛሬ ችግር ይቀርፋል።
ከዚህ ባሻገር የታክስ ከፋዩን ቁጥር በማሳደግ መንግስት የሚሰበስበውን የግብር መጠን ሊያሳድግ ይችላል። ይህም በአገራዊ ኢኮኖሚ ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል። ከመካከለኛ ጊዜ አኳያ መንግስት የሚሰበስበውን ግብር መጠን ከማሳደጉም በተጨማሪ የዋጋ ግሽበትን በማረጋጋት፣ የግምጃ ቤት ክምችት እጥረትን በመቅረፍና ኢንቨስትመንትን በማነቃቃት በኩል ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።
ከረጅም ጊዜ አንጻር የዲጂታላይዜሽን ስርዓት ዝርጋታን በማፋጠን ዘመናዊ የፋይናንስ ስርዓት እንዲዘረጋና ገንዘብ በባንክ ስርዓት ውስጥ ብቻ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ የገንዘብ ዝውውርና ቁጥጥር ፖሊሲ መሳሪያዎችን ያሳድጋል።
አሮጌው የብር ኖት በአዲሱ መተካት ከተጀመረ አንድ ወር አልፎታል። በቀሪዎቹ ሁለት ወራት አሮጌ የብር ኖቶች ሙሉ በሙሉ በአዲስ ተቀይረው ይጠናቀቃሉ። የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው አዲሱ የብር ኖት ለውጥ ከተጀመረ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ1 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ የባንክ አካውንት የተከፈቱ ሲሆን ከባንክ ውጪ በግለሰቦች እጅ ተከማችቶ የነበረ ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ባንክ እንዲገባ ተደርጓል።
ይህም ቀደም ሲል ከባንክ ውጪ ይንቀሳቀሳል ተብሎ ከሚገመተው 113 ቢሊዮን ብር ወደ 32 በመቶ ያህል ወደ ባንክ መግባቱን የሚጠቁም ሲሆን ለኢኮኖሚው ያለው አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም። በቀሪዎቹ ሁለት ወራት ወደ ባንክ የሚገባው የገንዘብ መጠን ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችልም ይታመናል።
ምንም እንኳን አዲሱ የብር ኖት ቅያሬ በአገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ፋይዳው ሰፊ መሆኑን ቢገለጽም በጥንቃቄ ካልተመራ ከአጭርና ከረጅም ጊዜ አኳያ መንግስትን ሊፈትኑ የሚችሉ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲተ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት አቶ ደረጄ ዮሃንስ ከኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በገጠር አካባቢዎች የባንክ ተደራሽነት ውስን ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት እንዲሰራጭ በማድረግ በኩል ክፍተት እንዳያጋጥም ካልተሰራ በዚህ ሂደት ህገ ወጥ የገንዘብ አንቀሳቃሾች አዲሱን የብር ኖት አስመስለው በፍጥነት ሊያትሙ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ ገና አዲሱን ብር በደንብ ሳያውቀው በህገወጥ መንገድ የታተመ የሃሰት የገንዘብ ኖት ተሰራጭቶ ህብረተሰቡን ሊያደናግር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ከዚህ በተጨማሪ በህገ ወጥ መንገድ ያከማቹትን ገንዘብ በቋሚ ንብረት ለመለወጥ የሚንቀሳቀሱትን ለመቆጣጠር ሲባል የተዘረጋው አሰራርም በተግባር በጥብቅ ክትትል ካልተደገፈ የሙስና ሂደቱ ውስብስብና በኔትወርክ የተጠላለፈ ስለሆነ በእጅ አዙር የሚደረጉ ሽያጮች ሊኖሩ ስለሚችሉ ተመልሶ የነበረውን ችግር ሊያባብስ ይችላል ይላሉ። ይህም ተመልሶ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ያደርጋል ባይ ናቸው።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ሙሀመድ አብራር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ የብር ኖት ለውጥ ለኢኮኖሚው አይነተኛ ሚና ቢኖረውም ወሳኝና ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊያመጣ የሚችለው ግን የፋይናንስ ስርዓቱን ማዘመን ነው።
ማህበረሰቡ ገንዘብ በጥሬ ከማንቀሳቀስ ይልቅ ባንኮችን በመጠቀም እንዲገበያይና አዳዲስ የፋይናንስ ዝውውር ሂደቶች እንዲጠቀም መስራት ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ይናገራሉ።
የግብይት ስርዓቱ ማዘመንና የገንዘብ ዝውውር በስርዓት እንዲመራ ማድረግ የመንግስት ገቢ ለማሳደግና ሕገ ወጥ ተግባራት ለመግታት ትልቅ መፍትሄ መሆኑን የሚገልፁት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ሙሀመድ፣ አሁን በአገሪቱ እየታየ ያለው ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር መንስኤው የፋይናንስ ስርዓቱ በትክክል ባለመመራቱ ስለመሆኑም አክለው ይገልጻሉ።
እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ምልከታ አዲሱ የብር ኖት ለውጥ የፋይናንስ ስርዓቱን ከማስተካለ ባለፈ በአገራዊ ኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ ነው። የብር ኖት ለውጡ ከተጀመረ ወዲህ የባንክ ተቀማጭ ገንዘብ ጭማሪ ማሳየቱ፣ አዳዲስ አካውኖች መከፈታቸው፣ የተጭበረበሩ የብር ኖቶችን ከገንዘብ እንቅስቃሴ ውጪማስወገድ ማስቻሉ ከጠቀሜታዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ይህ አዎንታዊ ፋይዳዎች እንደተጠበቁ ሆነው ዘላቂ መፍትሄው ህብረተሰቡ የባንክ አጠቃቀም ባህሉ እንዲጎለብት ማድረግ እና ከወረቀት የክፍያ ስርዓት ወደ ኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት መሸጋገር ነው። ስለሆነም የብር ኖት ለውጡ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ በቀሪዎቹ ጊዜያት ሁሉም አካላት ግልጽነትና ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መልኩ እንዲሰራና ዘላቂ መፍትሔዎች ላይ ከወዲሁ እንዲታሰብበት መልእክታችን ነው።