ቀጥታ፡

የአንበጣ መንጋ በኢትዮጵያ እስካሁን በ420 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ጉዳት አድርሷል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የበረሃ አንበጣ መንጋ እስካሁን በ420 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ጉዳት ማድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ገለጹ።

በክረምቱ የጎርፍ አደጋም 600 ሺህ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ ልዩ ስብሰባውን አካሄዷል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ የዓመቱን መንግሥትን የትኩረት አቅጣጫዎች አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የበረሃ አንበጣ መንጋ እያስከተለ ያለውን ውድመትና የመከላከል ሂደት አስመልክቶ ጥያቄዎች አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ከሰው ሰራሽ ችግሮች በተጨማሪ የአንበጣ መንጋ፣ ኮቪድ-19 ወረርሽኝና ጎርፍ የተፈጥሮ ፈተናዎች ገጥመዋታል ብለዋል።

ቀድመን ተንብየን ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን በመቀነስ ስራዎች ቢሰሩም መፈጠራቸውን ሳናውቅ አደጋ ከደረሰ በኋላ የመከላከል ብቻ ስራዎችን ለመስራት የሚያስገድዱ ነገሮች መታየታቸውንና ከነዚህም አንዱ የበረሃ አንበጣ መንጋ መሆኑን አመልክተዋል።

ከቀይ ባህር የተነሳው የበረሃ አንበጣ መንጋ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋርና ሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ የተለያዩ ዞኖች ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

የአንበጣ መንጋ የስጋት ቀጠና ተብለው 240 ወረዳዎችና 4 ሺህ 938 ቀበሌዎች ተለይተዋል ብለዋል።

የአንበጣ መንጋው እስካሁን ባስከተለው ውድመት በ420 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ጉዳት መድረሱንም አመልክተዋል።

አንበጣው የሚያደርሰውን ጉዳት ቀደም ብሎ ለመከላከል አውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮችን ተከራይቶ ለማስመጣት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በተለያዩ ችግሮች አለመሳካቱን ገልጸዋል።

ሆኖም የተወሰኑ አውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮች እንዲሁም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በማስገባት አንበጣውን የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ትናንት ማምሻውን የተወሰኑ አውሮፕላኖች የገቡ ሲሆን በዚህም ሳምንትም ተጨማሪ አውሮፕላኖች ይገባሉ።

ይሁንና በኬሚካል ርጭቱ ብቻ የአንበጣው መንጋውን መከላከል ስለማይቻል በማታ አንበጣው ካለበት ቦታ ሳይነሳ በባህላዊ መንገድ የማጥፋት ስራ ማከናወን ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

የበረሃ አንበጣ ጉዳይ መንግስት ጉዳዩን ቸል ብሎታል የሚለው ጉዳይ ግን ስህተት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

መንግስት የአንበጣ መንጋው እንዳይስፋፋና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ለረሃብ እንይጋለጡ የአደጋ መከላከል አቅምን የማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በተያዘው ዓመት 35 ሚሊዮን ኩንታል ተጨማሪ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ጠቅሰዋል።

በአንበጣ መንጋው ጉዳት የደረሰባቸውን አርሶ አደሮች ለመደገፍ መንግስት በጥናት እየለየ መሆኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመሆን የአየር መንገዱን የትናንሽ አውሮፕላኖች የመጠገን አቅም በማሳደግ ለኬሚካል ርጭት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተግባራት የመጠቀም ስራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በደረሱ የጎርፍ አደጋዎች 600 ሺህ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም