በአዲስ አበባ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነት ወደ 85 በመቶ ለማሳደግ ይሰራል---ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነት ወደ 85 በመቶ ለማሳደግ ይሰራል---ቢሮ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነት አሁን ካለበት 50 በመቶ ወደ 85 በመቶ ለማሳደግ እንደሚሰራ የከተማው አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው በቀጣይ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅዱ ላይ በዘርፉ ከተሰማሩ አካላት ጋር ዛሬ አካሂዷል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ታዜር ገብረእግዚአብሔር በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ቢሮው የዘርፉን ምርታማነት አሁን ካለበት በ35 በመቶ ለማሳደግ ጥረት ያደርጋል።
በዚህም የከተማዋን ነዋሪዎች የምርት አቅርቦትን ለማሻሻል እንደሚሰራ ተናግረዋል።
እንዲሁም ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡና ለዘርፉ ግብዓት የሚሆኑ ስትራቴጂያዊ ምርቶችንም አሁን ካለበት 30 በመቶ ወደ 60 በመቶ ለማሳደግም ታስቧል ብለዋል።
በሌላ በኩል ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ 500 ሚሊዮን ለማድረስ መታቀዱንም ተናግረዋል።
ዘርፉ ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አሁን ካለበት አራት በመቶ ወደ 14 በመቶ ለማሳደግ መታቀዱን አስታውቀዋል።
ዕቅዱ ከከተማዋ ብሎም ከአገሪቱ ፍላጎት ጋር እንደሚጣጣም አቶ ታዜር አስታውቀዋል።
ዘርፉ መሰረታዊ የኃይል ፣ የብድርና የመስሪያ ቦታ አቅርቦት፣የማስፈጸም አቅም ውስንነት ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና የሰለጠነና የበቃ የሰው ኃይል ችግሮች አሉበት ብለዋል።
ዕቅዱ ዘርፉን የሚያሳድጉ ምቹ ሁኔታዎችን በመለየት ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ አቶ ታዜር ተናግረዋል።
የበለፀጉ አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው ካለ አምራች ኢንዱስትሪ ዕድገት ለሥራ መስፋፋት፣ ለገቢ መጨመር፣ ለፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልና የአገር ብልፅግናን ማረጋገጥ አይቻልም።
በዘርፉ ዕድገት በማስመዝገብ ከበለፀጉ አገሮች መካከል ጃፓን ፣ ኮሪያና ታይዋን ተጠቃሽ ናቸው።