በደቡብ ክልል ዘላቂ ሠላምና ደህንነት ለማስፈን ህዝቡ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርግ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል ዘላቂ ሠላምና ደህንነት ለማስፈን ህዝቡ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርግ ተጠየቀ
ሀዋሳ ጥቅምት 9/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ዘላቂ ሠላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ህዝቡ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርግ ተጠየቀ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በምዕራብ ኦሞ ዞን ከተውጣጡ የህዝብ ተወካዮች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በባቹማ ከተማ ትናንት መክረዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በምክክር መድረኩ እንደገለጹት የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ መንግሥት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ሆኖም ካለ ህብረተሰቡ ተሳትፎ ዘላቂ ሠላምን እውን ማድረግ ስለማይቻል በዚህ ረገድ ህዝቡ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በተለይ በየደረጃው የሚገኘው ህብረተሰብ የአብሮነት እና መተሳሰብ ባህሉን እየጎለበተ ሲሄድ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።
በምክክር መድረኩ የተሳተፉ የዞኑ የህዝብ ተወካዮች ለአካባቢው ፀጥታና ደህንነት ጉዳይ ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ሠላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ ህብረተሰቡን በማስተባበር ለሰላም መከበር አበክረው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
በአካባቢያቸው የሚስተዋለው የመንገድ፣ ኤሌክትሪክ መብራት፣ ትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ችግር እንዲቃለልባቸው በመድረኩ አመልክተዋል።
አቶ ርስቱ በበኩላቸው በዞኑ እየተስተዋለ ያለውን የመሰረተ ልማት ችግር እንደ አንገብጋቢነቱ እየተለየ ከዞኑ አስተዳደር ጋር ተቀናጅተው ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ሆኖም በክልሉ መሠረተ ልማቶችን በሚፈለገው ልክ ለማሟላት የበጀት ውስንነት እንዳለ ጠቅሰው ያለውን ውስን ሀብት ወደ ልማት በማስገባትና ህብረተሰቡን በማስተባበር እንደሚሰራ አስረድተዋል።
በተለይ በጤና ተቋማት ውሰጥ የህክምና ግብዓቶችን ለማሟላትና በሰለጠነ የሰው ኃይል ለማደራጀት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የኤሌክትሪክ ተደራሽነት በተመለከተ በሁሉም አካባቢ የሚስተዋል ችግር በመሆኑ ለመፍታት መንግሥት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።