ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ዘንድሮ በገንዘብ፣ በኤሌክትሮ መካኒካልና በሲቪል ስራዎች የላቀ ስራ ይጠይቃል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9/2013 ( ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘብ፣ በቴክኒክ፣ በኤሌክትሮ መካኒካልና በሲቪል ስራዎች በተያዘው ዓመት የላቀ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ምን ይመስላሉ? በሚል ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ተነስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ በ2012 ዓ.ም የህዳሴ ግድብ ግንባታ አስመልክቶ ስኬታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።

የግድቡ ግንባታ ዋና ስራ በዘንድሮው ዓመት የሚቀጠል መሆኑን ገልጸው፤ የግንባታ ሂደቱ የሁሉንም ድጋፍና ጥረት ይጠይቃል ብለዋል።

የ2013 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በገንዘብ፣ በቴክኒክ፣ በኤሌክትሮ መካኒካልና በሲቪል ስራዎች ከባለፉት ዓመታት የላቀ ስራ የሚጠይቅ መሆኑንም አብራርተዋል።

በህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚንጸባረቁ ነገሮች በአንድ በኩል እድል በሌላ በኩል ክፋት ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እድሉ በግድቡ ስራ የተከናወኑ ስራዎች ትልቅ ትኩረት ማግኘታቸው ነው ብለዋል።

ያለው ክፋት ደግሞ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲስተጓጎልና እንዲበላሽ የሚፈልጉ ሃይሎች መኖራቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ከግራና ከቀኝ የሚመጡትን ነገሮች ትተን በሙሉ ልብ የተባበረ ክንድ የዘንድሮውን ዓመት የህዳሴ ግድብ  ስራዎች ማጠናቀቅ ይገባል ብለዋል።

ለግድቡ ግንባታ ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 69 ከተሞች የኤሌትሪክ ሃይል እንዲያገኙ መደረጉንና 12 መለስተኛ ከተሞች ከፀሐይ ሃይል የኤሌትሪክ ሃይል እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

12ቱ መለስተኛ ከተሞች በህዳር ወር አጋማሽ ከፀሐይ ሃይል የኤሌትሪክ ሃይል ሙሉ ለሙሉ እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ሰአት የ25 የፀሐይ ሃይል ፕሮጀክቶች ግንባታ በሂደት ላይ ሲሆን ይህም ከኤሌትሪክ ማስተላለፊያ ጋር ካልተገናኙ መስመሮች (ኦፍ ግሪድ) ሃይል ለማግኘት ለሚከናወነው ስራ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ከኤሌትሪክ ማስተላለፊያ ጋር ካልተገናኙ መስመሮች (ኦፍ ግሪድ) ሃይል መጠቀም የኤሌትሪክ ሃይል አማራጭን የሚያሰፋ ነው ብለዋል።

በተለይም በጤና ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በአነስተኛ ከተሞችና መለስተኛ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የኦፍግሪድ የሃይል አማራጭን ብንጠቀም የኤሌትሪክ ሃይል ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከሃይድሮ ፓውር፣ ከነፋስና እንፋሎት በበለጠ ከፀሐይ ሃይል ከፍተኛ እምቅ አቅም እንዳላትና በቀጣይ የፀሐይ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

የግሉ ዘርፍ በሃይድሮ ፓወር፣ በነፋስና በፀሐይ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እየገቡ እንደሆነና ያላውን ተሳትፎ እያደገ እንዲሄድ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከኤሌትሪክ ሃይል ያላትን እምቅ ሃብት ለመጠቀም የፕሮጀክቶችን አፈጻጸምና የአመራር የውሳኔ ሰጪነት አቅም ማሳደግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም