ህብረተሰቡ የኮሮና መከላከያ መመሪያዎችን ተግባራዊ እንዲያደርግ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች አስገነዘቡ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ የኮሮና መከላከያ መመሪያዎችን ተግባራዊ እንዲያደርግ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች አስገነዘቡ
ባህር ዳር ጥቀምት 8/2013 (ኢዜአ) ህብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ራሱንና ሌሎችን ከበሽታው ሊታደግ እንደሚገባ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች አሳሰቡ።
የኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ከአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ጋር በመተባበር "እናስታውሳችሁ" በሚል መሪ ቃል በኮሮና መከላከል ላይ ያተኮረ ትምህርታዊ ቅስቀሳ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በባህርዳር ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች እየተካሄደ ባለው ትምህርታዊ ቅስቀሳ የተሳተፈው አርቲስት ሱራፌል ተካ ህብረተሰቡ በጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት እየከፈለ ያለውን የህይወት ዋጋ ለመታደግ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግበሩ ተዘጋጅቷል ።
የኮሮና ቫይረስ በሽታ ስርጭት እየሰፋ ባለበት ወቀት የህብረተሰቡ መዘናጋት እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን ጠቁሟል ።
ህብረተሰቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በማድረግ ፣ ሳኒታይዘር በመጠቀምና እጅን በሳሙና መታጠብን በመተግበር ራሱንና ሌሎችን ከበሽታው ሊታደግ እንደሚገባ አስገንዝቧል ።
"ህብረተሰቡ መከላከያ ዘዴዎችን በመተው መዘናጋት እያሳየ ነው" ያለው ደግሞ ኮሜዲያን በረከት በቀለ ነው።
"በሽታው የግድ እኛን እስኪይዘን ድረስ መጠበቅ የለብንም" ያለው ኮሜዲው ህብረተሰቡ ከእለት ወደ እለት የሚያሳየው አላስፈላጊ መዘናጋት የቫይረሱ ስርጭት እንዲጨምር ምክንያት እንደሚሆን አመላክቷል ።
ህብረተሰቡ በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ የመከላከያ መመሪያዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ እራሱን፣ ቤተሰቡንና ሌሎችን ከበሽታው አንዲጠብቅ መልዕክት አስተላክፏል ።
"በህብረተሰቡ ውስጥ በኮሮና በሽታ ዙሪያ እየተስተዋለ ያለው መዘናጋት የበሽታውን አሳሳቢነት እንዲጨምር አድርጎታል" ያሉት ደግሞ የክልሉ ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ ናቸው።
"በተለይ ትምህርት ሊከፈት ነው ከተባለ ወዲህ ኮሮና የለም የሚሉ ሰዋች ተበራክተዋል" ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ባንጻሩ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ ስለመምጣቱ መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ተናግረዋል ።
የክልሉ መንግስት በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ከመስራት ጀምሮ የለይቶ ማቆያና የህክምና ቦታዎችን የማስፋፈት ስራ እያከናወነ መሆኑን አመላክተዋል ።
"ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ በራሱ አቅም ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ችላ በማለት ለአላስፈላጊ መስዕዋትነት እየተዳረገ ነው" ብለዋል።
"ትምህርትም ሆነ ሌሎች የልማት ስራዎች እንዲቀጥሉ የተደረጉት ሳይሰራ መኖር ስለማይቻል ነው "ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ ጥሪ አቅረበዋል ።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ "ስለበሽታው አሰከፊነት አጽንዖት ለመስጠት ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ማካሄድ አስፈልጓል" ብለዋል ።
"ቫረሱን ለመከላከል እጅን መታጠብ፣ አካላዊ እርቀትን መጠበቅ፣ አፍና አፍንጫን በጭንብል መሸፈንና ሳኒታይዘር መጠቀም አይነተኛ መንገዶች ቢሆኑም ህብረተሰቡ ተግባራዊ እያደረጋቸው አይደለም" ብለዋል።
ህብረተሰቡ የጥንቃቄ መንገዶቹን በመተግበር እራሱንና ሌሎችን ከበሽታው እንዲጠብቅ አስገንዝበዋል ።
በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እየተደረገ ያለው የቅስቀሳ ስራ ከነገ ጀምሮ ለሚከፈተው የትምህርት ስራና ለዘርፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው" ያሉት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ ናቸው።
ወላጆችና ተማሪዎች በጤናና በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የሚሰጡትን የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ተግባራዊ በማድረግ በሽታውን የመከላከልና የትምህርት ስራውን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል ።
ተማሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በማድረግና የግል ንጽህናን በመጠበቅ ኮሮናን እንዲከላከሉ ዶክተር ይልቃል መልእክት አስተላልፈዋል።
በባህር ዳር በከተማ ዋና ዋና መንገዶችና ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች በማርሽ ባንድ የታጀበ የኮሮና መከላከል ትምህርታዊ የቅስቀሳ ስራ ተካሂዷል ።