ቀጥታ፡

ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራሁ ነው- ፍርድ ቤቱ

ድሬዳዋ ጥቅምት 8/2013 (/ኢዜአ/) በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አስታወቀ። 

ፍርድ ቤቱ ከ38 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ ያስገነባውን ባለ 5 ፎቅ አገልግሎት መስጫ ህንጻ ዛሬ አስመርቋል።

ህንጻው የሰነዶች ማከማቻ፣የችሎትና ሁለገብ አዳራሾች፣ በደህንነት ከሜራ የታገዘ ልዩ የህጻናት ችሎት፣ የታራሚዎችና የምስክር ማቆያ፣ ቤተመጻህፍት፣ ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት መስጫዎችን ያካተተ መሆኑ ተነግሯል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሀመድ በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ እንደገለጹት የህንጻው መገንባት ተገልጋዩ ፍትህ ለማግኘት የሚያባክነውን የምርትና የሥራ ጊዜ ማስቀረት ያስችላል፡፡

"ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት በፍትህ አሰጣጥ ላይ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቀነስ  እንደሚያግዝ  አመላክተዋል ።

ፍርድ ቤቱ አሰራርና አደረጃጀቱን በማሻሻልና በቴክኖሎጂ በመታገዝ የተጓተቱ የክርክር ሂደቶችን በአጭር ጊዜ ብይን እንዲሰጣቸው እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

ቀደም ሲል በዓመት 3ሺህ 500 ፋይሎች ይታዩ እንደነበር አስታውሰው በተጠናቀቀው በጀት አመት ለ7 ሺህ ፋይሎች ብይን መስጠቱን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

ከአስተዳደሩ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ጋር በመሆን ባለጉዳዮች ለይግባኝ ጉዳያቸው ክትትል ወደ አዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ሣይጓዙ በቴክኖሎጂ ችሎት እንዲከታተሉ እየተደረገ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋጡም ሙስጠፋ ህንጻውን  ከመረቁ በኃላ እንደተናገሩት የፍርድ ቤቱን የዳኝነት ሥልጣን ለመጨመር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ተግቶ መስራትይገባል ።

"ለገጠሩ ህብረተሰብ  የፍትህ-ተደራሽነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል" ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ አሠራሩን በማዘመንና ብቃት ባለው የሰው ኃይል በመታገዝ ለፍትህ- ስርትህ መስፈን ይበልጥ መትጋት እንዳለበት አፈ-ጉባኤዋ አስገንዘበዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም