ቀጥታ፡

የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት 193 አሽከርካሪዎቹን ሸለመ

አዲስ አበባ   ጥቅምት 8 /2013 (ኢዜአ) የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ለተከታታይ አምስት ዓመታት የትራፊክ አደጋ ያላደረሱ 193 አሽከርካሪዎችን ሸለመ።

የድርጅቱ ማኔጅመንትና ሰራተኞችለ''ገበታ ለሀገር'' ፕሮጀክት ማስፈፀሚያና ለሌሎች ተቋማት ከ4 ነጥብ 6ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።

ከአምስት ዓመታት በላይ በሚነዱትም ሆነ በሌሎች አሸከርካሪዎች ላይ ምንም ዓይነት አደጋ ሳያደርሱ ላሽከረከሩ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልመዋል።

እንዲሁም ለአራት ዓመታት ምንም ዓይነት አደጋ ሳያደርሱ ላሽከረከሩ የብር፣ ለሶስት ዓመታት ያለ አደጋ ላሽከረከሩ ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸልመዋል።

በተጨማሪም የድርጅቱ የሰሜን ቀጣና ማስተባበሪያ ዋንጫ ሽልማት ተሸልሟል።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ወልደየስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ከአምስት ዓመታት በፊት በ100 ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ለመንግሥት ሰራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት የጀመረው ድርጅት ትርፋማ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከመንግሥት እንደ መነሻ የተሰጠውን ብድር ገንዘብ የአውቶቡሶቹን ቁጥር 500 ማድረሱ እንደሚያስመሰግነው ተናግረዋል።

የድርጅቱ ተሽከርካሪዎች በከተማዋ በመንግሥት ሰራተኞችና ነዋሪዎች ዘንድ የሚታየውን የትራንስፖርት እጥረት ለማቃለል እየሰሩ ናቸው ብለዋል።

የድርጅቱ አሽከርካሪዎች በሚያደርጉት ጥንቃቄ ራሳቸውንና ሌሎችን  ከአደጋ በመጠበቅ ለድርጅቱ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ እድገት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያላትን ትልቁ ሃብት የሰው ሃብት ከአደጋ ለመጠበቅ አሽከርካሪዎቹ ሲያደርጉ ለቆዩት አሽከርካሪዎች የተሰጠውን ዕውቅና ''ተገቢ ''ይሉታል።

የድርጅቱ አሽከርካሪዎች  ከኮቪድ 19 መከሰት ጋር ተያይዞ የመንግሥት ሰራተኛው በሥራ ገበታው ላይ በሰዓቱ እንዲገኝ በማድረግ የዜግነት ግዴታቸውን እንደተወጡም መስክረዋል።

በተለይም ''እንደርሳለን'' በሚል የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ  የተቀመጠውን አገራዊ ግብ እውን ከማድረግና የኮሮና ወረርሽኝን ተከላክሎ በጥንቃቄ ከማሽከርከር ተሳትፎ ማድረጋቸውን በመጠቆም።

የሲቪል ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬሕይወት ትልቁ በበኩላቸው  ድርጅቱ ከመስከረም 5ቀን 2007 ጀምሮ ድርጅቱን በማቋቋም የመንግስት ሰራተኞች በወቅቱ በስራ ገበታቸው ላይ እንዲገኙ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የድርጅቱ አሽከርካሪዎች ሥነ ምግባርን በተላበሰ መልኩ በመንቀሳቀስ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በመቀነስ ረገድ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ በበኩላቸው የድርጅቱ አሽከርካሪዎች ጠንቃቃ በመሆናቸው በድርጅቱ የሚሰጠው የመድን ካሳ መቀነሱን አስታውቀዋል።

ለዚህ ውጤት ደግሞ ተቋማቱ  በቅንጅት ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የድርጅቱ ማኔጅመንትና ሰራተኞች  በሽልማት ፕሮግራም ላይ ለ''ገበታ ለሀገር'' ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ከ4ነጥብ6 ሚሊዮን ብር በላይ፣ለካንሰር ሕሙማን ማህበር 20ሺህ ብር፣ለልብ ሕሙማን ማዕከል ደግሞ 50 ሺህ ብር ለግሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም