ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመናዊ አሰራሮችን እየተገበረ ነው

አዲስ አበባ   ጥቅምት 8 /2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ይዞ ለመጓዝ  ዘመናዊ አሰራሮችን እየተገበረ መሆኑን አስታወቀ።

ዓለም አቀፉን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ  አየር ክልላቸውን የዘጉ አገሮች በሮቻቸውን እየከፈቱ ነው።

ኢትዮጵያ ከያዝነው ወር ጀምሮ ለቱሪዝም በሮቿን ስትከፍት አየር መንገዱም ወቅቱ የሚጠይቀውን ዝግጅት በማድረግ አገልግሎቱን ባዘመነ መንገድ እንደሚቀጥል ገልጿል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የዲጂታል ማርኬቲንግ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ምህረተአብ ተክላይ ለኢዜአ እንደገለጹት አየር መንገዱ የዲጂታል አሰራር በመከተል ተወዳዳሪነቱን ይዞ ለመጓዝ እየሰራ ነው።

በተለይ ዓለም አቀፍ  መንገደኞች የኮሮና ቫይረስ ስጋትን ለመቀነስና ስጋት ሳይሰማቸው እንዲጓጓዙ የሰጠው የኮቪድ-19 ዋስትና አየር መንገዱ ቀዳሚ አድርጎታል ይላሉ። 

የኦን ላይን ቪዛ አሰራርን ሥራ ላይ በማዋል ደንበኞች ባሉበት ሆነው ከአራት እስከ ስድስት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ በእጅ ስልካቸው ቪዛ የሚያገኙበት ሁኔታ እንደፈጠረ ተናግረዋል።

ዘመናዊና ግዙፍ በቴክኖሎጂ የታገዘ ኤርፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመሩም ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ ቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ የዲጂታል አገልግሎትም እያደገ መጥቷል ያሉት አቶ ምህረተአብ፣አንድ አራተኛ የሚሆነው የሽያጭ አገልግሎት በእጅ ስልክ(በሞባይል) እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የአገር ውስጥ ደንበኞች የሞባይል የኦንላይን ሽያጭ አገልግሎት 43 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል።

እንዲሁም 70 በመቶ የሚሆኑት ደንበኞች ደግሞ በሞባይል የኦን ላይን አገልግሎት ጉዞአቸውን እንደሚያረጋግጡ ገልጸዋል።

ይህም ደንበኞች ወደ ዲጂታል አገልግሎት ''በስፋት እየገቡ መሆኑን ያሳያል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ በቀዳሚነት የተቀመጠ፣በዓለምም ምርጥ ከሚባሉ አየር መንገዶች አንዱ ለመሆን የሚገኝ የአየር ትራንስፖርት ሰጪ ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም