በፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሚመራው የኤርትራ ልዑክ የኢትዮጵያ ጉብኝቱን አጠናቆ ተመለሰ - ኢዜአ አማርኛ
በፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሚመራው የኤርትራ ልዑክ የኢትዮጵያ ጉብኝቱን አጠናቆ ተመለሰ
ሃምሌ 9/1010 በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የኤርትራ ልዑክ በኢትዮጵያ ያደረገውን የሶስት ቀናት ጉብኝቱን ዛሬ አጠናቅቆ ወደ ሀገሩ ተመልሷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድም ለኤርትራ ልዑካን ቡድን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው አሸኛኘት አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሁለቱም ሀገራት ከፍትኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ዛሬ ማለዳ የኤርትራ ኤምባሲ በይፋ ተከፍቷል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈው ቅዳሜ የኤርትራ ልዑካን ቡድንን በመምራት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል። ቅዳሜ በነበረው ስነስርዓት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፥ ከሰዓትም የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን መጎብታቸው ይታወሳል። በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ከ25 ሺህ በላይ ህዝብ በታደመበት የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ማብሰሪያ መድረክ ተካሂዷል። በዕለቱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በመልክ፣ በአንድነታችን ተመሳሳይ ነን፤ ይህን አንድ የሆነ ህዝብ ማንም ሀይል ሊለያይ አይችልም ብለዋል። የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ተለያይተው በነበሩበት ወቅት የተቃጠለውን ጊዜ ለማካካስ እንሰራለን ነው ያሉት ።