ቀጥታ፡

የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ወደ ሹመት መምጣት ለዴሞክራሲ ዕድገት ጠቃሚ ነው

ጥቅምት 08/2013 (ኢዜአ) የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ወደ መንግሥት ሥልጣን በሹመት መምጣት ሊበረታታ የሚገባው እና ለዴሞክራሲያዊ ዕድገት ጠቃሜታ ያለው መሆኑ ተነገረ።

በሀገር ጉዳይ በአንድነት ተጋግዞ መሥራት እንደሚቻል ማሳያ ምሳሌ ነውም ተብሏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ተሹመው መሥራት መጀመራቸውን ተከትሎ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በሰጡት አስተያየት የተፎካካሪ ፖለቲካ አመራሮችን በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በአመራርነት እንዲሠሩ መደረጉ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትና አሳታፊነትን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ዋና ጸሐፊ አቶ በቀለ ነጋ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሾሙ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በሙያቸውና በክህሎታቸው ለቦታው የሚመጥኑ መሆናቸው ተረጋግጦ የሚሾሙ ከሆነ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።

ባልተለመደ መልኩ ለተፎካከሪዎች ዕድል የመስጠት ጅማሮው የሚበረታታና አሳታፊ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሚሾሙት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ሥራውን መምራት አቅም አላቸው ወይ የሚለው ሊጤን የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ለቦታው የሚመጥኑ ሆነው ከተገኙ መመደባቸው አስፈላጊም ተገቢም ነው የሚሉት አቶ በቀለ፤ የሹመቱ ዕድል መሰጠቱ ተገቢና ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው።

መሠረታዊ ችግራችን ከሚሾመው ሰው ሳይሆን የሚሾመው ሰው ሥራውን በብቃት ይመራዋል ወይ ብሎ መጠየቅ ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ ገልጸው፤ እንደ ሀገር ማንኛውም የሥራ ሹመት ወይም ሃላፊነት ሲሰጥ የግለሰቡ የሙያ ብቃትና ችሎታ መሠረት ተደርጎ ብቻ መሆን አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በነበረው የፖለቲካ ልምድ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በመንግሥት ሹመት የመስጠት ልምድ እንዳልነበረና አሁን ላይ የተጀመረው አሳታፊነት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ መጠናከር ትልቅ አስተዋፅዖ የሚያበረክት መሆኑን ገልፀዋል።

የተፎካካሪ ፖለቲካ ታርቲ አመራሮች በተለያዩ የመንግሥት ሥራ ሃላፊነት ላይ መሾማቸው ለዴሞክራሲው መጎልበት ጥሩ ሚና አለው። መንግሥትን የሚቃወሙና የተለያየ የሀሳብ ልዩነት ያላቸው ብቁና ቦታውን የሚመጥኑ ሰዎች የተለያዩ ተቋማት ውስጥ በሃላፊነት መሾማቸው በፓርቲዎች መካከል በጋራ የመሥራት ልምድ ሊያጠነክርና ተቀራርበው በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲግባቡ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግስት ለተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ይህንን መሰል እድል መስጠቱ በጣም የሚያስደስት እርምጃ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ዳንኤል፤ ተግባሩ በሀገር ጉዳይ ላይ በአንድነት ተጋግዞ መሥራት እንደሚቻል በምሳሌነት መጥቀስ እንደሚቻልም ማሳያ ነው።

ሹመቶቹ ለዴሞክራሲያዊና ለሰብዓዊ መብቶች መረጋገጥ አይነተኛ ሚና እንዳላቸው የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ ሹመቱ በራሱ የፖለቲካ ተሳትፎ መብት መሆኑንና በልዩነት ውስጥ የሚፈጠሩ የተለያዩ ሰብዓዊ ቀውሶችም ከመከሰታቸው በፊት ተቀራርቦ ለመነጋገርና ለመግባባት በር የሚከፍት መሆኑን ያስረዳሉ።

የሰዎች መብት እንዲጣስ የሚያደርገው የከረረ የፖለቲካ አስተሳሰብ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ዳንኤል ይህንን ለማርገብ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

በቅርቡ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት ዶክተር አረጋዊ በርሄ በመንግሥት የተለያዩ ተቋማት ላይ የፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተሹመው መሥራት መጀመራቸው የሚበረታታና አስደሳች መሆኑን ገልፀው፤ እሳቸው የተሰጣቸው ሃላፊነት በትክክልና በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸው መግለፃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም