ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የህዝቡ ተሳትፎና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት- አስተያየት ሰጭዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የህዝቡ ተሳትፎና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት- አስተያየት ሰጭዎች
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7/2013 ( ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የህዝቡ ተሳትፎና ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ አካላት ገለጹ።
የግድቡ ግንባታ ስኬት ትውልዱ የታሪክ አሻራውን አሳርፎ የሚያልፍበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑንም አስተያየት ሰጭዎቹ ተናግረዋል።
አስተዯየት ሰጪዎች እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከልማት ፕሮጀክትነቱ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ብራንድ የሚያጎላ ነው።
የግድቡ መጠናቀቅ በተለይ በውጭው ዓለም ስለ ኢትዮጵያ ያለውን የተሳሳተና የተዛባ ምልከታ የሚያስተካክል ሲሆን ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የመከወን አቅማችንንም የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጭው ትውልድ ለማስረከብና በኤሌክትሪክ ሃይል እጦት በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ብርሃን እንዲያገኙ ለማስቻል ለግድቡ ግንባታ ድጋፍና ጥረታችን መቀጠል አለበት ብለዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ኢትዮጵያዊያን አገር ወዳድነቸውን በተግባር የሚገልጹበት፣ የአንድነት፣ የሉአላዊነት መገለጫና በጋራ የሚከወን የሁሉም ሃብት መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጰያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ እዘዘው፤ ኢትዮጵያዊያን ህዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ ታሪክ ሰርተን ማለፍ አለብን ነው ያሉት።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ በህዳሴ ግድብ እስካሁን ያስመዘገብነው ውጤት ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
የግድቡን ግንባታ በማጠናቀቅም ውጤታማነታችንን አስጠብቀን መቀጠል አለብን ብለዋል።
ባለፈው ዓመት የህዳሴ ግድቡ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት እውን ከሆነ በኋላ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠላቸው ይታወቃል።
በተያዘው ዓመት ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት የሚደረግ ሲሆን ሁለቱ ተርባይኖችም ሃይል ማመንጨት ይጀምራሉ።
የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ እስኪውል ድረስ ዜጎች የሚያደርጉትን ድጋፍና እገዛ አጠናክረው እንዲቀጥሉም አምባሳደር ኢብራሂም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያና የኢጋድ አባል አገራት የነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ እንዳሉትም በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የህዝቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
''አሁን የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች አሉ፣ በወጣቶች፣ በሴቶችና በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ግድቡ የኔነው ባይነት እየተቀሰቀሰ አለ ይሄን የተቀሰቀሰውን አጋግሎ መሄድና በተለይ ለዓለም ማስጨበጥ'' ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዬ ዋና ጸሃፊ ሊቀ-ትጉሃን ታጋይ ታደሰም ተመሳሳይ ሃሳብና የጋራ ልቦና ይዘን መጓዝ አለብን ብለዋል።
"ሁሉም ተርባይኖች ስራ ጀምረው በኢትዮጰያ ያለው ከ50 በታች የነበረው የሃይል አቅርቦት ከ80 እስከ 90 በመቶ እስኪያድግ ድረስ የምንችለውን ድጋፍ እንዳናቋርጥ በኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማትና በራሴ ስም ጥሪዬንም አቀርባለሁ" ሲሉም ተናግረዋል።
አቶ መላኩ እዘዘው በበኩላቸው የንግዱ ማህበረሰብ አቅሙ በፈቀደ መጠን ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ህብረተሰቡ በአገር ውስጥም በውጭም አገር ያለው ህዳሴ ግድብን ለመጨረስ በሚደረገው አገራዊ ተሳትፎ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪዬን ማስተላለፍ እንፈልጋለን።''
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ "ግብጾች በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚቻልበት ወቅት ነው ብለው የሚያስቡበት፤ የነሱን ጥረት የእነሱን ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉትን ሴራ ማክሸፍ የምንችለው አንድነታችን ሲጠናከር ነው" ብለዋል።
የግድቡ ጉዳይ የጋራ የአገር ጉዳይ መሆኑንና የሚኖሩ ልዩነቶችን ምክንያት በማድረግ ገሸሽ የምናደርገው ጉዳይ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁናዊ አፈፃፀሙ 76 በመቶ መድረሱ ይታወቃል።