የጊኒር ከተማ አስተዳደር በማህበራት ለተደራጁ 696 ነዋሪዎች የቤት መስሪያ ቦታ ሰጠ

ጊኒር፣ ጥቅምት 7/2013(ኢዜአ) በምስራቅ ባሌ የጊኒር ከተማ አስተዳደር መምህራንን ጨምሮ በህብረት ስራ ማህበራት ለተደራጁ 696 ነዋሪዎች የቤት መስሪያ ቦታ መስጠቱን የከተማው የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የረዥም ጊዜ ጥያቄ ሆኖ የቆየው የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ እጥረት መፍትሔ በማግኘቱ መደሰታቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሙዘሚል ናሲር እንደገለጹት የነዋሪውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል በማህበር  ለተደራጁ 29 ማህበራት 140 ሺህ ካሬ የሚጠጋ መሬት ለመኖሪያ ቤት መስሪያ ተሰጥቷል።

ተደራጅተው የመስሪያ ቦታ የተሰጣቸው  መምህራንና ሌሎችም የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም ሌሎች ነዋሪዎችን ጨምሮ ለ696 ሰዎች መሆኑን ተናግረዋል።

ተደራጅተው ያላገኙ ማህበራትም በአጭር ጊዜ ውስጥ መሬት ተዘጋጅቶ እንደሚተላለፍላቸው አመልክተው፤ በቀጣይም ለነዋሪዎች የመሬት ፍላጎት በአግባቡ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

የጊኒር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሐመድ አብዱልቃድር በበኩላቸው መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መሬት የሌላቸው ወጣቶችና የመንግስት ሰራተኞች በመለየት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ብሏል፡፡

አስተዳደሩ የከተማውን ነዋሪ የረዥም ጊዜ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመለየት ደረጃ በደረጃ ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

ከከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ፋጡማ ሀሰን በሰጡት አስተያየት ለረዥም ጊዜ ስንጠይቅ የነበረው የቤት መስሪያ ቦታ ዛሬ ምላሽ በማግኘቱ ተደስቻለሁ ብለዋል፡፡

"በቀን ሰራተኝነት በማገኘው ገቢ ቤተሰቤን ከማስተዳደር ባለፈ ለኪራይ ቤት 1 ሺ ብር ወጪ አደርጋለሁ ፤ አሁን በተሰጠኝ መሬት ላይ ቤቴን በመገንባት ለመኖር ተዘጋጅቻለሁ" ያለው ደግሞ ወጣት ሚፍታህ አብዱልቃድር ነው፡፡ 

ሌላው ቦታ ያገኙት  አቶ ማህሙድ ሁሴን በበኩላቸው ከ2009 ዓ.ም ጀምረው የሚጠበቅባቸውን ቁጠባ አጠናቀው የቤት መስሪያ መሬት ሲጠይቁ እንደነበር አውስተዋል፡፡

"የረዥም ጊዜ ጥያቄያችን በዛሬው እለት ምላሽ በማግኘቱ ደስተኛ ነኝ፤ የረዱንን የአስተዳደሩን አካላት እናመሰግናለን’" ብለዋል፡፡

ወጣት አቤል ሙላቱ  የተሰጠው የቤት መስሪያ ቦታ ለቤት ኪራይ የሚያወጣውን ገንዘብ እንዲቆጥብ ከማገዝ ባለፈ የራሱን  ሀብት ለማፍራት እንደሚያስችለው ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም