ኤርትራ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን እንደገና ከፈተች - ኢዜአ አማርኛ
ኤርትራ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን እንደገና ከፈተች
አዲስ አበባ ሀምሌ 9/2010 ኤርትራ ከ19 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን እንደገና ከፈተች። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኤምባሲውን ቁልፍ ተረክበዋል። የኤርትራ ኤምባሲ ሁለቱ አገራት ወደ ጸብ እስከገቡበት ድረስ በአገልግሎት ላይ የነበረ ሲሆን ላለፉት 19 አመታት ዝግ ሆኖ ቆይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት በኤርትራ ባደረጉት ጉብኝት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በነበራቸው ውይይት ሁለቱም የዘጓቸውን ኤምባሲዎች ለመክፈት በተስማሙት መሰረት ኤርትራ ኤምባሲዋን ዛሬ ከፍታለች። በአዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ በግምት 6 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው የኤምባሲው ህንፃ በ1950ዎቹ የተገነባ ሲሆን ህንጻው በደርግ ዘመን በአዋጅ ቁጥር 26/1967 ዓ.ም መሰረት በመንግስት የተወረሰ ነበር፡፡ ከወታደራዊው መንግሥት ውድቀት በኋላ ደግሞ የኤርትራ ኤምባሲ ሆኖ ያገለግል ነበር፡፡ በሁለቱ አገራት በተፈጠረው ጦርነትና ዜጎችን ከሁለቱም አገራት ማስወጣት ሳቢያ ኤምባሲው የተዘጋ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ዋና መሥሪያ ቤት ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን እንደገና በማደሳቸው የወጣቶች ፌዴሬሽንን በማስለቀቅ በድጋሚ በኢትዮጵያ የኤርትራ ኢምባሲ ሆኖ እንዲያገለግል ተሰጥቷል።