ቀጥታ፡

በመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ተይዘው እስካሁን ያልለሙ ቦታዎች ግንባታ ሊካሄድባቸው ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7/2013 (ኢዜአ) በፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ተይዘው እስካሁን ያልለሙ ቦታዎች ግንባታ ሊካሄድባቸው መሆኑን የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ሌንሣ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት በፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ተይዘው እስካሁን ያልለሙ ቦታዎች ላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ታቅዷል።

በመሆኑም በመጪዎቹ አምስት ዓመታት 18 የተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚገነቡ ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ የሶስት ፕሮጀክቶች ግንባታ ይጀመራል ተብሏል።

ለዚህም ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት ፕሮጀክቶቹን በፍጥነት እና ጥራት ማልማት የሚችሉ ባለሃብቶችን ለመሳብ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የሚገነቡት ፕሮጀክቶች በጤና፣ በቱሪዝም፣ በሆቴል፣ በግብርና፣ በቤቶች ግንባታና በትምህርት ዘርፎች ላይ መሆኑንም የሚከናወኑ መሆናቸውንም ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

የፕሮጀክቶቹ መገንባት ለተለያዩ ሴክተሮች አቅም ማጠናከሪያ እንዲሁም ለሀገሪቷ የኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ለግንባታው ተጨማሪ ሃብት ማስገባት የሚችሉ አልሚዎችን ማሳተፍ ዋነኛው ትኩረት ይሆናልም ነው ያሉት።

የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን በዛሬው ዕለት " በፕሮጀክት መገምገሚያ ቀመር " ዙሪያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አንድ አካል በመሆን በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 ከ3 ዓመት በፊት ነው የተቋቋመው፡፡

የፌዴራል መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን የፌዴራል መስሪያ ቤቶችንና የመንግስት የልማት ድርጅቶችን መሬት እንዲያስተዳድርም ነው የተመሰረተው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም