የኮሮና ቫይረስን መከላከል ታሳቢ ያደረገ ትምህርት ለመጀመር እየተዘጋጀን ነው -- ርዕሰ መምህራን - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮና ቫይረስን መከላከል ታሳቢ ያደረገ ትምህርት ለመጀመር እየተዘጋጀን ነው -- ርዕሰ መምህራን
ጥቅምት 7/2013 (ኢዜአ) ኮሮና ቫይረስ መከላከልን ታሳቢ ያደረገ ትምህርት ለመጀመር እየሰሩ መሆናቸውን የግልና የመንግስት ትምህርት ቤቶች ገለጹ።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ትምህርትና ዳግም ለማስጀመር እያደረጉት ባለው ዝግጅት ላይ ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ተማሪዎች ከኮሮና ቫይረስ ተጠብቀው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የገለጹት የሆሊ ሴቨር የተባለ የመጀመሪያ ደረጃ የግል ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ወይዘሮ አዳነች ተፈራ ናቸው።
ትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን ለወረርሽኙ በማያጋልጥ መልኩ ዝግጁ የማድርግ ስራ እየሰራ መሆኑን ርዕሰ መምህሯ ተናግረዋል።
እንደ ወ/ሮ አዳነች ገለጻ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በአንድ ክፍል ውስጥ ከ20 እስከ 25 ተማሪዎች ብቻ እንዲማሩ ይደረጋል።
ስለ ወረርሽኙ መከላከያ መንገዶች ግንዛቤን የሚያሳድጉ ባነሮችን በማዘጋጀት በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ የመስቀል ተግባርም እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
መምህሩ ለተማሪው፣ ተማሪው ለመምህሩ፣ መምህሩ ለመምህሩ፣ ተማሪው ለተማሪው ምክኒያት አይሁን በሚል መርህ የመማር መስተማር ስራው የሚካሄድ ይሆናል ብለዋል።
በእያንዳንዱ ተማሪ መቀመጫ መካከል ያለው ርቀትም ከአንድ ሜትር ያላነሰ ሆኖ የተዘጋጀ መሆኑንና መምህራንም በተመሳሳይ ርቀታቸውን ጠብቀው ትምህርት እንዲሰጡ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል።
የተማሪዎችን ጥግግትን ለመቀነሰም ትምህርት በፈረቃ እንደሚሰጥ ወይዘሮ አዳነች ገልጸዋል።
ውሃና ሳሙናንና ሌሎች የቫይረሱ መከላከያ ቁሳቁሱት መሟላታቸውንና ማንኛውም ሰው ወደ ግቢው ሲገባ ሙቀቱ እየተለካ እንዲስተናገድ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በተማሪ ቤተሰቦች የሚስተዋለውን ስጋት ለመቅረፍ ልጆቻቸውን ለማስመዝገብ ሲመጡ ትምህርት ቤቱ ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት እንዲመለከቱ ተደርጓል።
በግቢው የተመለከቱት ነገርም ከነበረባቸው ስጋት ነጻ እንዳደረጋቸና ወደፊትም ስጋት እንዳያድርባው በየጊዜው እየመጡ ምልከታ እንዲያደርጉ ይደረጋል ብለዋል።
እያንዳንዱ ወላጅ ለልጁ ከመማሪያ ቁሳቁሶች ባልተናነሰ መልኩ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ እንዲያዘጋጅ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መሰራቱን ርዕሰ መምህሯ ተናግረዋል።
ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ከገቡ በኋላ ድንገት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ችግር ቢያጋጥም ትምህርት ቤቱ የሚተካ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ለመምህራን ፣ ለአስተዳደር ሰራተኞችና ለወላጅ ኮሚቴዎች ኮሮናን መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መድረክ ተዘጋጅቶ ውይይት መደረጉን የገለጹት ደግሞ በሆሊ ሴቨር ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ወይዘሮ አስናቀች በቀለ ናቸው።
ወይዘሮ አስናቀች ህጻናት ከሚያዩት ነገር የመማር አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ለህጻናቱ አርአያ እንዲሆኗቸው ይደረጋል ነው ያሉት።
ወላጆች ልጆቻቸውን በጥንቃቄ ለት/ቤቱ እንዲያስረክቡ ትምህርት ቤቱም በጥንቃቄ ከትምህርት በኋላ መልሶ እንዲያስረክብ ይደረጋል ብለዋል።
ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያደርጋሉ አያደርጉም የሚለው በቀጣይ ትምህርት ቢሮ በሚያወርደው አቅጣጫ የሚወሰን ይሆናል ብለዋል ።
ኮሮና ቫይረስ የመከላከሉን ስራ እየሰራን የመማር ማስተማር ስራውን ለማከናወን ተዘጋጅተናል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ እድገት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ተፈራ መኮንን ናቸው።
ከዚህ በፊት የመማሪያ ክፍሎችን በውሃና በሳሙና የማጽዳት ስራ የተሰራ ሲሆን በቅርቡም የኬሚካል ርጭት የሚደረግ ይሆናል ብለዋል ።
ትምህርት ቤቱ ትምህርት ቢሮ ከሚያቀርብለት የወረርሽኙ መከላከያ ቁሳቁሶች በተጨማሪ ሌሎች አቅርቦቶችን ለማሟላት ከበጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጋር እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በሳምንት ስድስት የትምህርት ቀናት የሚኖሩ ሲሆን ተማሪዎች በፈረቃ ተከፋፍለው ሶስት ሶስት ቀናት እንዲማሩ ይደረጋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በበኩሉ የ2013 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራ ከኮሮና ስጋት በጸዳ መልኩ ለመጀመር እንዲቻል ከኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስትር በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።
ቢሮው የንቅናቄ ሰነድ በማዘጋጀት በመንግስትም ሆነ በግል ትምህርት ቤቶች ወረርሽኙን ለመከላከል ምን ምን ተግባራት መከናወን አለባቸው በሚሉ ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በቢሮ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት እንደገለጹት ከከተማ ምክር ቤቶች ፣ከማህበራት አባላት ፣ከመምህራን ማህበር፣ከባለሃብቶች ፣ከሀይማኖት አባቶችና ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር ውይይት ተደርጎ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል።
እንዲሁም ከወረዳና ከክፍላ ከተማ ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች፣ከመምህራን፣ ከሱፕር ቫየዘሮች ጋር በጋራ ምክክር መደረጉን ተናግረዋል ።
በአሁኑ ሰዓት የውሃ እጥረት እና ተጨማሪ ግንባታ የሚያስፈልጋቸው ትምህርት ቤቶችን በመለየት የውሃ አቅርቦቱ እንዲሟላ እንዲሁም ተጨማሪ ክፍሎች እንዲገነቡ እየተደረገ እንደሚገኝም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
የመንግስትም ሆኑ የግል ትምህርት ቤቶች የጤና ባለሙያዎችን እንዲመደቡ መመሪያ ወጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የግል ትምህርት ቤቶችን በተመለከተ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቀቁሞ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
ኮሚቴው ትምህርት ቤቶችን ይገመግማል ያበቃል ለመማር ማስተማር ስራው ዝግጁ መሆናቸው ሲያረጋግጥ ለትምህርት ቢሮ በሚያቀርበው ሪፖርት መሰረት እንዲጀምሩ ይደረጋል ብለዋል።
ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ያደርጋሉ አያደርጉም የሚለው የዘርፉ ባለሙያዎች በሚያቀርቡት ምክረ-ሃሰባ መሰረት ወደፊት የሚወሰን ይሆናል ብለዋል አቶ አበባ።