የአማራ ክልል ለቅዱስ ላሊበላ ቅርሶች ግንባታ 30 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ለቅዱስ ላሊበላ ቅርሶች ግንባታ 30 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ
ባሕርዳር፣ ጥቅምት 7/2013 (ኢዜአ) የአማራ ክልላዊ መንግሥት የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን የግንብ አጥርና ሌሎች ግንባታዎች 30 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ።
በክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ዋለ ጥጋቡ ለኢዜአ እንደገለጹት የገንዘብ ድጋፉ የተደረገው የክልሉ መንግሥት ሥራውን ለማገዝ በገባው ቃል መሰረት ነው።
የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ጥገና በፈረንሣይ መንግሥት ሙሉ ወጪ የሚደገፍ በመሆኑ የደብሩ አስተዳደር ባለፈው ዓመት ያስጀመረውን የግንብ አጥርና ሌሎች ሥራዎች እንዲያግዝ ክልሉ ዘንድሮ 30 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።
የአጥሩ መታጠርም ቅርሶቹን በዘላቂነት በመንከባከብ ለጎብኝዎች ምቹ፣ ሳቢና ማራኪ በማድረግ የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም ከኮሮና ቫይረስ በኋላ ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ በግንባር ቀደምትነት ከሚጎበኙ ሀገራት አንዷ ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ያግዛል።
የቅዱስ ላሊበላ ደብር አስተዳዳሪ አባ ጽጌሥላሴ መዝገቡ በበኩላቸው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን ለማስጠገን የተለያዩ ተቋማት ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን አውስተዋል።
አሁን ላይ በፈረንሣይ መንግሥት ጥገናው የሚካሄድ በመሆኑ ቃል የተገነባውን ገንዘብ በማሰባሰብ የቅርሶቹን ዙሪያ በጥርብ ድንጋይ የማጣርና ደረጃውን የጠበቀ ሙዚየም ግንባታ ለማከናወን እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከ42 ሄክታር በላይ ስፋት የሚሸፍነው የቅርሱ አጥር ዲዛይን ቀድሞ በመጠናቀቁ ባለፈው ዓመት ከዘይት ወይራ እስከ ችፍርጎች ማዞሪያ በደብሩ የውስጥ ገቢ ማስገንባታቸውንና ሥራው ዘንድሮም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
በጥርብ ድንጋይ የአጥር ግንባታም በየቀኑ ከ50 ለሚበልጡ ሰዎች የሥራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመው ክልሉ በሰጠው ድጋፍ ዘንድሮ ደረጃውን የጠበቀ የሙዚየም ግንባታ ለማስጀመር የዲዛይን ሥራው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሙዚየሙ መገንባት የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ከ800 ዓመታት በላይ ያከማቹትን ጥንታዊ ቅርሶች አሰባስቦ ለቱሪስቶች ክፍት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
የቅርሱ ጥገና ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ሙያተኞች ኮሮና ሳይበግራቸው ቅርሱ ያለበትን የሙቀት፣ ቅዝቃዜ፣ የተፈለፈለበት አለት ሁኔታን እያጠኑ ናቸው ብለዋል።
ጥናቱን በሦስት ወር ውስጥ በማጠናቀቅ ወደ ተግባራዊ የጥገና ሥራው እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ቀደም ሲል ለቅርሱ አጥር ግንባታና ሌሎች ሥራዎች የክልሉ መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣንና የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ከ72 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መገባታቸውም ተመልክቷል።