በደቡብ ወሎና ጌዴኦ ዞኖች ትምህርት ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎና ጌዴኦ ዞኖች ትምህርት ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው
ደሴ፣ ዲላ ፣ ጥቅምት 7/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎና ጌዴኦ ዞኖች የኮሮና ቫይረስን በመከላከል የዘመኑን የመማር ማስተማር ስራ ለማስጀመር ቅደመ ዝግጅት እየተደረጉ መሆኑ ተገለጸ።
የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጀማል አበጋዝ ለኢዜአ እንደተናገሩት ለትምህርት ዘመኑ እየተደረገ ያለው ዝግጅት በዞኑ በሚገኙ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ645 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ነው።
ለዚህም እስካሁን ከ520 ሺህ በላይ ተማሪዎች መመዝገባቸውን አመልክተዋል።
የቀሪዎችም ምዝገባ በማጠናቀቅ የተሻለ ዝግጅት ያደረጉ ትምህርት ቤቶች ኮሮናን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የማስተማር ስራ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከዞኑና አልማ በተገኘ 160 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ 882 መማሪያ ክፍሎችና ሌሎችም ግብዓቶች እየተሟሉ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከዚህ በፊት ግንባታቸው የተጀመሩ ትምህርት ቤቶችና ማስፋፊያ ህንጻዎች ፈጥነው እንዲያልቁ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ሦስት አዲስ ትምህርት ቤቶችና ከ600 የሚበልጡ መማሪያ ክፍሎች ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል።
በአንድ ክፍል ከ30 ተማሪዎች በታች መማር እንዲችሉ ግብዓቶች እየተሟሉ ነው ያሉት ኃላፊው ሦስት ሺህ የሚጠጋ አዲስ ወንበርና ጠረጴዛም ከሰሞኑ ለትምህርት ቤቶች ማሰራጨታቸውን ገልጸዋል፡፡
"አንድ ማስክ ለአንድ ተማሪ" በሚል መሪ ሀሰብ በየወረዳው ግንዛቤ ተፈጥሮ እየተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመው፤ እስካሁን ከ150 ሺህ በላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡
በትምህርት ቤቶች የውሃ ፣ መፀዳጃ ቤት፣ መጻህፍት፣ ቤተ ሙከራና ሌሎች እጥረቶች እንዳይኖሩም ከወዲሁ የማመቻቸት ስራ እየተከናወነ ነው፡፡
ትምህርቱን እስከ ሦስት ፈረቃ ለመስጠት ተጨማሪ 563 መምህራንን የመቅጠር ስራ መጀመሩንም ኃላፊው አመልክተዋል።
በኮምቦልቻ ከተማ የሠርደም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ መሃመድ ሰይድ በበኩላቸው 1 ሺህ 79 ተማሪዎችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ለኮሮና መከላከያ ቁሳቁስ እየተመቻቸ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለያዩ አካባቢዎች የእጅ መታጠቢያዎች መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡
ትምህርት ቢዘጋም ለፈተና ሲዘጋጅ መቆየቱንና አሁን ደግሞ ትምህርት ለመጀመር መሰናዳቱን የገለጸው ደግሞ በሐይቅ ከተማ የ12ኛ ክፍል ተማሪ አዩብ አሊ ነው፡፡
"ከኮሮና ራሴን ጠብቄ ለመማር የትምህርትና የኮሮና መከላከያ ቁሳቁሶችን አዘጋጅቻለሁ" ብሏል፡፡
በተመሳሳይ በጌዴኦ ዞን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የመማር ማስተማር ስራ ለማስጀመር ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የትምህርት ስራ አመራሮች ገልጸዋል።
የዲላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ወንዶሰን ዳካ ለኢዜአ እንዳሉት ትምህርት ለመጀመር እስካሁን ከ2 ሺህ 100 በላይ ተማሪዎች ምዝገባ ተካሂዷል።
በትምህር ቤቱ የጥንቃቄ መስፈርትን ባሟላ መልኩ ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመው በተለይ ከዚህ ቀደም ትምህርት ይሰጥባቸው ከነበሩ 30 ክፍሎች ሌላ ለተለያዩ አገልግሎቶች ይውሉ የነበሩ 10 ተጨማሪ ከፍሎች ለመማር ማስተማር ስራ ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
በግቢው ውስጥ በቂ የውሃ አቅርቦት እንዲኖር ነባር ቧንቧዎችን ከማሳደስ ባለፈ የተለያየ መጠን ያላቸውን 24 የውሃ ማከማቻ ሮቶዎች በመማሪያ ከፍሎች አቅራቢያ ለአገልግሎት መሰናዳታቸውን አስረድተዋል።
በዲላ ዙሪያ ወረዳ የሃንዲዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ጋሻው በየነ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱን ለተማሪዎች ምቹ ከማድረግ አንስቶ እስከ መምህራን ድልደላ ድረስ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
ትምህርት በሁለት ፈረቃ ከመሰጠቱ ጋር ተያይዞ በተለይ በሒሳብና ቋንቋ ትምህርቶች ማጋጠሙን የተናገሩት ደግሞ በገደብ ከተማ የገደብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መመህር የሆኑት ሃብታሙ ጎበና ናቸው።
ችግሩንም ለመፍታት ከከተማው ከትምህርት ጽህፈት ቤት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው ሌሎች ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አስረድተዋል።
የጌዴኦ ዞን ትምህረት መምሪያ ተወካይ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በዞኑ ከ360 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እስካሁን ከ90 በመቶ በላይ መከናወኑን ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቶች ትምህርት ለማስጀመር እያደረጉት ባለው ዝግጅት ዙሪያ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በ300 ትምህርት ቤቶች በተደረገ ምልከታ ያሉበት ቁመና አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ በተጨማሪ መማሪያ ክፍሎች ግንባታና መምህራን ለማሟላት የተደረጉ ጥረቶች የተቋረጠውን ትምህርት ለማስቀጠል የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
መንግስት ባስቀመጠው ጊዜ ገደብ የመማር ማስተማር ስራው ሲጀመር የኮሮና ቫይረስ የጥንቃቄ መመሪያዎችን እንዲተገበሩ የትምህርት ባለድርሻ አካላት መከታተል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።