ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨሰትመንት በመሳብ ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ሆነች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨሰትመንት በመሳብ ከምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ስትሆን ከአፍሪካ አምስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገልጿል፡፡

የቻይና ኩባንያዎችም በአገሪቱ የኢንቨሰትመንት ዘርፍ ቀዳሚ ተዋናዮች በመሆን 43 ቢሊዮን ብር ፈሰስ አድርገዋል ተብሏል።

ከቻይናና ከሌሎች አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚፈሰው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መጨመሩን ተከትሎ "ኢትዮጵያ ለውጭ ኢንቨስተሮች ምቹ መዳረሻ እየሆነች መምጣቷን" የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር መኮንን ኃይሉ ለዥንዋ ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያና ቻይና ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብርና ትሥሥር አላቸው፤ ይህን ተከትሎ በርካታ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ተሰማርተዋል" ሲሉ ገልጸዋል።

"በኢትዮጵያ ፈሰስ የተደረገውን የቻይናውያንን ኢንቨስትመንት ከሌሎች አገራት ጋር ስናነጻጽረው የላቀ ነው።

በዚህም ኩባንያዎቹ በአገሪቱ ዕድገት ላይ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ ነው" በማለት ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

"በርካታ ኩባንያዎች ከእስያ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ ቻይና፣ አውሮፓና አውስትራሊያ ወደ አገሪቱ እየገቡ ነው።

ነገር ግን በርካታዎቹ ኢንቨስተሮች ከቻይና የሚመጡ ናቸው የዚህ ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ ያላት እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም ነው" ሲሉ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ኮንፈረንስ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሠረት ኢትዮጵያ ባላት አዎንታዊ የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታ በምሥራቅ አፍሪካ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ቀዳሚዋ አገር መሆኗን ጠቅሷል።

ከአፍሪካ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ኮንጎና ሞሮኮን በመከተል አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

በርካታ የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የመረጡበት ምክንያት አገሪቱ ምቹ የሆኑ የኢኮኖሚ መዳረሻዎች ስላሏት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኝ ኢኮኖሚ ባለቤት ከመሆኗ ባለፈ ምቹ የሆነ የገበያ ዕድል ያለባት አገር ናት።

ከዚህ ባለፈ ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በጣም አስፈላጊ የሆነውን መሠረተ ልማት አሟልታ መያዟንም አብራርተዋል።

"በኢትዮጵ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በቻይናውያን ኩባንያዎች ተይዘው ወደ ሥራ የገቡና በዝግጅት ላይ የሚገኙ 1 ሺ 564 ፕሮጀክቶች ይገኛሉ።

እነዚህ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ውስጥ ዋነኛ ተዋናዮች ሲሆኑ በፕሮጀክት ቁጥርና በፋይናንስ አቅርቦት ቀዳሚ ናቸው" ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ከዥንዋ ጋር ቆይታ ያደረጉት ዳይሬክተሩ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ዘላቂ በሆኑ የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ኢንቨስት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ከኮሚሽኑ የተገኙ ቁጥሮች እንደሚያሳዩት ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ወይም እ.ኤ.አ ከ1998 እስከ ማርች 2020 ባለው ጊዜ 1 ሺ 564 የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ላይ ተሳትፈዋል።

ከነዚህ መካከል በርካቶቹ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን ጥቂቶቹ በሂደት ላይ ይገኛሉ ተብሏል።

ከተጠቀሱት 1 ሺ 564 የቻይናውያን የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት መካከል 987 በምርት ላይ የሚገኙ ሲሆን 187 ወደ ምርት ለመግባት በዝግጅት ላይ ናቸው።

የተቀሩት 391 ፕሮጀክቶች ደግሞ በቅድመ ትግበራ ሂደት ላይ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

ወደ ሥራ ከገቡት 1 ሺ 564 ፕሮጀክቶች መካከል 1 ሺ 113 ፕሮጀክቶች አገሪቱ ቅድሚያ ሰጥታ በምትሰራበት በማምረቻ ዘርፍ ላይ ተሰማርተዋል።

የቻይና ባለሀብቶች በስፋት የተሰማሩባቸው ሌሎች ዘርፎች ግንባታ፣ ሪል ስቴት ልማት፣ ሆቴል፣ ግብርና፣ የማስጎብኘት አገልግሎት፣ ኮሙኒኬሽን፣ ትምህርትና የማዕድን ዘርፍ መሆናቸው ተብራርቷል።

ከኮሚሽኑ የተገኙ ቁጥሮች እንደሚጠቁሙት የፕሮጀክቶቹ አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ዋጋ 43 ነጥብ 1 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም