ማዕከሉ የአንበጣ መንጋን ለመከላከል አርሶ አደሩ አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከሉ የአንበጣ መንጋን ለመከላከል አርሶ አደሩ አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ አሳሰበ
አርባ ምንጭ፣ ጥቅምት 7/2013 (ኢዜአ) የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል አርሶ አደሩ አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ የአርባ ምንጭ እጸዋት ጥበቃ ማዕከል አሳሰበ።
የማዕከሉ ሥራአስኪያጅ አቶ ሙላለም መርሻ ለኢዜአ እንደተናገሩት ማዕከሉ በሚንቀሳቀስባቸው ስድስት ዞኖችና አራት ልዩ ወረዳዎች የአንበጣ መንጋ በተደጋጋሚ ይከሰታል።
በተለይ ዓምና በዚህን ወቅት በጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ዳውሮ፣ ደቡብ ኦሞና ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም በኮንታ፣ ደራሼ፣ አሌ እና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች መከሰቱን አስታውሰዋል።
ሆኖም የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ በኬሚካል ርጭትና በባህላዊ ዘዴ ለመከላከል ጥረት በመደረጉ በእጸዋት ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉን አስረድተዋል።
በተያዘው ዓመትም በሃገሪቱ ምስራቅና ሰሜኑ ክፍል የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር መንግስት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
መንጋው በባህሪው በነፋስ ኃይል በየትኛውም አቅጣጫ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊዛመት የሚችል በመሆኑ ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህ ረገድ ማዕከሉ አገልግሎት በሚሰጥባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎችና የግብርና ባለሙያዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያና ቅስቀሳ ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የአንበጣ መንጋው እንደወትሮው በሰሜን ኬኒያና ሶማሊያ በኩል ሊከሰት ስለሚችል አርሶ አደሩና ሌላው የህብረተሰብ ክፍል አካባቢውን ነቅቶ እንዲጠብቅ ስራ አስኪያጁ አሳስበዋል።
መንጋው ድንገት ቢከሰት ለመከላከል እንዲቻል በቂ ኬሚካልና አንድ የመርጫ አይሮፕላን በአርባ ምንጭ አውሮፕላን ማረፊያ መዘጋጀቱን ጠቅሰው ህብረተሰቡም በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ከወዲሁ እንዲዘጋጅ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጋሞ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ካልሳ በበኩላቸው በዞኑ ከ91 ሺህ ሄክታር በላይ በመኸር ወቅት የለማ ሰብል እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአንበጣ መንጋ በለማው ሰብል ጉዳት ሳያስከትል ለመቆጣጠር አርሶ አደሩ ማሳውን ዘውትር እንዲከታተል የማስገንዘብ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።
የአንበጣ መንጋ ቢከሰት በባህላዊ መንገድ መከላከል ስለሚችሉበት ዘዴ በስልጠና ግንዛቤ ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የዘይሰ ድምቢሌ ቀበሌ አርሶ አደር አባተ አልዳዳ ናቸው።
ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ የመከላከል ልምድ እንዳላቸው ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ማሳቸውን ከተባዩ ለመከላከል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በጋሞ ዞን ቁጫ ወረዳ የጋሌ ቀበሌ የግብርና ባለሙያ አቶ ኤሊያስ ግላ የአንበጣ መንጋው በነፋስ በመታገዝ በቀን እስከ 300 ኪሎ ሜትር የመብረር አቅም እንዳለው አስረድተዋል።
በአካባቢው ድንገት ቢከሰት አርሶ አደሩ በባህላዊ መንገድ በመረበሽ ለማባረር እንዲዘጋጅ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።