የበረሃ አንበጣ እያደረሰ ያለውን ውድመት ለመከላከል የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የበረሃ አንበጣ እያደረሰ ያለውን ውድመት ለመከላከል የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል
አዲስ አበባ ጥቅምት 6/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ በሰብሎች ላይ እያደረሰ ያለውን ውድመት ለመከላከል ሁሉም ርብረብ አንዲያደርግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።
የተፋሰሶች ልማት ከፍተኛ ምክር ቤት 8ኛ መደበኛ ጉባዔውን በዛሬው እለት በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የጉባኤው ዋነኛ ትኩረትም የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ፣ የጎርፍ አደጋንና የእምቦጭ አረምን ማስወገድ ላይ ያተኮረ ነበር።
በጉባዔው ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንደገለጹት በኢትዮጵያ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ በተለይ በደረሱ ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ውድመት እያስከተለ ይገኛል።
የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል መንግስት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው ኬሚካል የሚረጩ አውሮፕላኖችን ከውጭ አገር ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሆኖም አንበጣውን በመከላከል ሂደት ሁሉም አካላት የድርሻቸውን አንዲወጡም ጠይቀዋል።
በእስካሁኑ ሂደት ማህበረሰቡ አንበጣውን ለመከላከል በየአካባቢው ያደረገውን ትግልም አድንቀዋል።