96 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አዲሱ የብር ኖቶች ተሰራጩ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6/2013(ኢዜአ) 96 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የአዲሱ የብር ኖቶች ለባንኮች መሰራጨታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

ከ100 ሺህ ብር በላይ የአሮጌ የብር ኖቶች መቀየሪያ ጊዜ ዛሬ እንዳበቃና እንደማይራዘም ተገልጿል።

ለአዲሱ የብር ኖት ቅያሪ ለጸጥታ ማስከበር ስራ የተቋቋመው የፌደራል ኮማንድ ፖስት የአንድ ወር አፈጻጸሙን የተመለከተ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሶቹን የብር ኖቶች ይፋ ካደረጉ በኋላ የብር ኖት ቅያሬው መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም መጀመሩንና ዛሬ አንድ ወር ማስቆጠሩን ገልጸዋል።

ከሁለት ቀናት በፊት ባለው መረጃ ወደ 31 ቢሊዮን አሮጌ የብር ኖቶች ወደ ባንኮች መግባታቸውንና የ96 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አዲሱ የብር ኖቶች በኢትዮጵያ በሚገኙ ባንኮች ሁሉም ቅርንጫፎች መሰራጨታቸውን አመልክተዋል።

ከሁለት ቀን በፊት ባለው መረጃ 920 ሺህ ሰዎች አዲስ የባንክ ሂሳብ መክፈታቸውን ተናግረዋል።

ከ100 ሺህ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ያላቸው በእጃቸው የሚገኘውን አሮጌ የብር ኖት የሚቀይሩበት የጊዜ ገደብ ዛሬ እንደሚጠናቀቅና የመቀየሪያ ጊዜው እንደማይራዘም ጠቁመዋል።

ከነገ ጀምሮ በባንኮች የብር ኖት ቅያሪ የሚደረግላቸው ከ100 ሺህ ብር በታች ያላቸው ሰዎች ብቻ እንደሆኑና ከ100 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ይዘው የሚገኙ ግለሰቦች ገንዘባቸው ተወርሶ ለመንግስት ገቢ ይደረጋል ብለዋል።

ከ100 ሺህ ብር በታች የገንዘብ ቅያሪው ለሁለት ወራት እንደሚቀጥል ገልጸው አፈጻጸሙ እየታየ የጊዜ ገደቡ ሊያጥር እንደሚችልም ነው ዶክተር ይናገር ያብራሩት።

ባንኩ በቀሩት ጊዜያት በአርሶና አርብቶ አደሩ እጅ የሚገኘውን ገንዘብ የመቀየር ስራ ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ገንዘቡን እንዲቀይርም ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት ከ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን አዲሱን የብር ኖቶች ማሳተሙንና አጠቃላይ የብር ኖቶቹ ያላቸው ዋጋ 262 ቢሊዮን ብር መሆኑን አስታውሰዋል።

አሮጌውን ብር ለመቀየር የሚያስችል በቂ የአዲሱ የብር ኖት ክምችት እንዳለም አክለዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ በበኩላቸው የአዲሱ የብር ኖት ቅያሪ የታለመትን አላማ እያሳካ ነው ብለዋል።

የብር ኖት ቅያሪው መደበኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በተለይም መደበኛ የምርት ሽያጭና የግብይት ልውውጥ እንዲያድግ በማድረግ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት በኩል ውጤታማ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

የአዲሶቹ የብር ኖት ቅያሬ የአንድ ወር አፈጻጸም ስኬታማ የሚባል መሆኑን ገልጸው የብር ኖት ቅያሪው በዘላቂነት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም