የበረራ የምግብ መስተንግዶዎችን በአገር ውስጥ ለመሸፈን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
የበረራ የምግብ መስተንግዶዎችን በአገር ውስጥ ለመሸፈን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ ጥቅምት 6/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ወቅት የሚቀርቡ የምግብ መስተንግዶዎችን በአገር ውስጥ ምርቶች ለመሸፈን የሚያስችል ስምምነት ከአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ጋር ተፈራረመ።
ትብብሩ የጥራት ደረጃቸው ከፍ ያለ ምግቦችን ለዓለም አቀፍ መንገደኞች ከማቅረብ ባሻገር አምራች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።
ስምምነቱ ለአርሶ አደሩ እና በግብርና ውጤቶች ንግድ ላይ የተሰማሩ አካላትን ወደ አዳዲስ ገበያዎች እንዲደርሱ ያደርጋል ተብሏል፡፡
በዚህም የተጠቀሱት አካላት በየአመቱ እስከ 10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ እንዲገኙ የሚያግዛቸው ሲሆን አየር መንገዱ ደግሞ የአገር ውስጥ የግብርና ምርቶችን እንዲጠቀም እንደሚያስችለው ተገልጿል።
የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤይድ) ለአርሶ አደሮቹ በመደበው ሶስት ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የመነሻ ካፒታል የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት አየር መንገዱ በሚፈልገው ደረጃ መጠኑንና ጥራቱን የጠበቀ የምግብ አቅርቦት እንዲሰጡ እንደሚያስችል በመግለጫው ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አዲሱ የትብብር መስክ በአየር መንገዱ እና በተራድኦ ድርጅቱ መካከል ያለውን ትስስር ያጠናክራል።
አየር መንገዱ ለአለም አቀፍ መንገደኞቹ ጥራቱን የጠበቀ የበረራ ላይ የምግብ አገልግሎት እንዲሰጥ ከማስቻሉ በላይ ለአርሶ አደሩ እና በግብርና ውጤቶች ንግድ ላይ ለተሰማሩ አካላት የገበያ ትስስርን ይፈጥራል ብለዋል፡፡
አየር መንገዱ ከውጭ ለሚያስገባው የምግብ አቅርቦት በአመት እስከ አንድ ቢሊዮን ብር እንደሚያወጣ የገለፁት አቶ ተወልደ ይህን በአገር ውስጥ መተካት መቻሉ የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ ሚናው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር በበኩላቸው፤ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የተፈረመው ስምምነት እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ታላላቅ ድርጅቶች በአገር ውስጥ ባሉ የንግድ ዘርፎችና ግለሰቦች ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን ቢያፈሱ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል የሚያሳይ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ለሌሎች ዘርፎች ምሳሌ መሆን የሚችል እውነተኛ አገር በቀል የኢኮኖሚ ስኬትን ያረጋግጣል ሲሉ ነው የገለጹት።
የትብብር ስምምነቱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በአገር ውስጥ አምራቾች እና በአርሶ አደሩ መካከል ትስስር በመፍጠር የግብርና ምርቶቻቸውን ለአየር መንገዱ እንዲያቀርቡ የሚያደርግ ይሆናል።
ስምምነቱ እንደ አውሮጳዊያን አቆጣጠር እስከ 2022 ድረስ የሚዘልቅ መሆኑ በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡