በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ላገገሙ አቅመ ደካሞች ግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ላገገሙ አቅመ ደካሞች ግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገ
ሐረር፣ ጥቅምት 6 /2013 (ኢዜአ) የሐረሪ ክልል የምግብ ዋስትናና አደጋ መከላከል ጽህፈት ቤት በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ላገገሙ አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች ግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
የገንዘብ ድጋፉ ካጋጠማቸው ወቅታዊ ችግር ለማለፍ እንደሚያግዛቸው የህብረተሰብ ክፍሎቹ ለኢዜአ ገልጸዋል ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊና የክልሉ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ኑረዲን ኢሳቅ በጀነላ ወረዳ ዛሬ በተካሄደው የድጋፍ ስነ ስርአት ላይ እንደገለጹት የገንዘብ ድጋፉ የተደረገው በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ላገገሙ 238 አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች ነው።
የህብረተሰብ ክፍሎቹ በኮቪድ- 19 ተይዘው ማቆያ የነበሩና በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ የሚተዳደሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
"በክልሉ በዘጠኙም ወረዳዎች ነዋሪ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎቹ በቫይረሱ መያዘቸውን ተከትሎ ያጋጠማቸውን ወቅታዊ ችግር መቋቋም እንዲችሉ የገንዘብ ድጋፉ ተደርጓል" ብለዋል ።
ከአለም የምግብ ድርጅት የተገኘው ገንዘቡ ለህብረተሰብ ክፍሎቹ በነፍስ ወከፍ 2ሺህ 100 ብር ድጋፍ እንዲደርሳቸው መደረጉን ተናግረዋል ።
የጀኔላ ወረዳ ነዋሪ ባሻ ግርማ በቫይረሱ ተይዘው ለ17 ቀን በማቀቆያ እንደነበሩ አስታውሰዋል ።
"አቅመ ደካማ በመሆኔ በቶሎ ወደ ስራ አልገባሁም፤ የተደረገልኝ የገንዘብ ድጋፍ ያጋጠመኝን ወቅታዊ ችግር ለማለፍ ይረዳኛል" ብለዋል ።
"በተቻለኝ አቅም ቫይረሱን ለመከላከል እያስተማርኩ እገኛለሁ" ያሉት ደግሞ የወረዳው ነዋሪ አቶ ናስር ደንቦባ ናቸው።
የገንዘብ ድጋፉ ችግራቸውን እንደሚያቃልልላቸው በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል ።