ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንግስትና የህዝብ ንብረት የዘረፉ አመራሮች ተጠያቂ ማድረጉን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6/2013(ኢዜአ) የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስትና የህዝብ ንብረት ላይ ዝርፊያ የፈጸሙ አመራሮች ተጠያቂ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

9 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በሚገመት የሙስና ወንጀል ላይ የምርመራ ስራ እያከናወነ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ በሩብ ዓመቱ ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልከቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጋር በተያያዘም 504 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡

የሙስና ወንጀሉን በሚመለከትም ክስ ለመመስረት የሚያስችል የኦዲት ሪፖርት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ በመግለጫው ተነስቷል፡፡

በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግስቴ እንዳሉት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር 270 ሚሊዮን ብር በላይ በመንግስትና ህዝብ ንብረት ላይ ዝርፊያ የፈጸሙና ተጨባጭ ማስረጃ የተገኘባቸው አመራሮችን ተጠያቂ አድርጓል፡፡

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጋር በተያየዘ 504 ሰዎች በቁጥጥር ውለዋል፡፡

ከነዚህ መካከል 232 የሚሆኑት የሰውና ሰነድ ማስረጃ ምስክርነት ተሰጥቶባቸው በዐቃቢ ህግ ቃል የተሰማባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በአጠቃላይ ስምንት ሺህ 668 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው በአራት ሺህ 249ኙ ላይ ማስረጃ እንደተገኘባቸው ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ በነበረው ብጥብጥና አለመረጋጋት 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን የሚገመት ንብረት እንደወደመም ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ ከባድ ወንጀሎች በአገር ውስጥና በአገር ውጭ ሲፈለጉ ነበሩ 96 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንደዋሉም አስታውቀዋል፡፡

አጠቃላይ ከአርቲስቱ ግድያ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ውለው ማስረጃ ያልተገኘባቸው አካላት እንዲፈቱ መደረጉንም አስገንዝበዋል፡፡

ኮሚሽኑ ወንጀሉን ለመፈጸም ተልእኮ ወስደው ሲንቀሳቀሱና ሲያደራጁ የነበሩ 1 ሺህ 105 ግለሰቦችን በመፈለግ ላይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሩብ ዓመቱ በአጠቃላይ በፌዴራልና በክልል ደረጃ 559 መዝገቦችን በማደራጀት ክስ የመመስረት ሂደት መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ በሩብ ዓመቱ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ተገኝቶባቸው የመጨረሻውን ክስ ለመመስረት የሚያስችል መስፈርት ያሟሉ 501 መዝገቦች ለጠቅላይ ዐቃቢ ህግ መቅረባቸውንም አረጋግጠዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ታላላቅ አገራዊ ጉዳዮችን የያዙ 1 ሺህ 711 ተጠርጣሪዎች መዝገብ ተከፍቶባቸው በኮሚሽኑ የምርመራ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ምክትል ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

የኦዲት ሪፖርቶችንና ከተለያዩ ተቋማት ከሚመጡ ማስረጃዎች በስተቀር አብዛኞቹ መዝገቦች የሰውና የሰነድ ማስረጃዎቻቸው ተጠናቋል ብለዋል፡፡

በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ኢ-ህገመንግስታዊ እንቅስቃሴ ባደረጉ አካላት ላይ የዞኑን አመራሮቹን ጨምሮ በአጠቃላይ 20 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው የክስ ሂደታቸው እየታየ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዞኑም በአጠቃላይ ከአራት ሺህ በላይ የሚሆኑ የቀድሞ ሰራዊት አባላት፣ ከመከላከያ፣ ከፖሊስና ከክልሉ ልዩ ኃይል የተሰናበቱ አካላት መደበኛ ባልሆነ መንገድ የዞኑን ጸጥታ እናስከብራለን የሚል ህገ-ወጥ ሰልፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የወንጀል ድርጊታቸው ጭካኔ የተሞላበት ግድያ፣ ዝርፊያና ታክስ ስወራ የፈጸሙ 86 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም በኮሚሽኑ መግለጫ ተመላክቷል፡፡

ከአሻራ፣ የወንጀል ስፍራ፣ ከባዮ ኬሚስትሪ እና ሌሎች ታያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘም ከባለጉዳይ ለኮሚሽኑ በሩብ ዓመቱ 21 ሺህ 456 መቅረባቸውና 21 ሺህ 433ቱ የፎረንሲክ ምርመራ ተጠናቀው ለተገልጋዮች ማሰጠታቸው ተነግሯል፡፡

ኮሚሽኑ በመንግስትና ህዝብ ንብረት ላይ ዝርፊያ በሚፈጽሙ አካላት ላይና ሰላማዊ እንቅስቃሴን በሚያውኩ አካላት ላይ በቀጣይነት ያለው ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም