የመድኃኒት ህጋዊነትን የሚያረጋግጥ መተግበሪያ ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የመድኃኒት ህጋዊነትን የሚያረጋግጥ መተግበሪያ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ ጥቅምት 6/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የመድኃኒት ህጋዊነትን የሚያረጋግጥ 'አይ ቬሪፋይ' የተሰኘ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ ይፋ አደረገ።
መተግበሪያው ህገ-ወጥ የመድሃኒት ዝውውርና ደህንነትን የሚያመለክትና የሚቆጣጠር ነው ተብሏል።
መተግበሪያውን በይፋ ያስጀመሩት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ እንደገለጹት በአገሪቱ የመድሃኒት አቅርቦት በመጠንና በአይነት እየጨመረ መጥቷል።
ይህም ለህገ-ወጥ የመድሃኒት ንግድ በር ከመክፈቱ ባሻገር ህብረተሰቡን ለጎንዮሽ የጤና ጉዳት እየዳረገው ይገኛል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ችግሩን ለመቅረፍ የመድሃኒትን ህጋዊነት የሚያረጋግጥ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ ስራ ላይ ማዋሉን አስታውቀዋል።
መተግበሪያው ጥራት፣ደህንነትና ፈዋሽነት የጎደላቸው መድኃኒቶች በገበያ ላይ ከመዋላቸው በፊት የትና በማን ተመርቶ እንደተሰራጨ በግልጽ ያስቀምጣል ብለዋል።
በተጨማሪም መድሃኒቱ በየትኛው ተቋም አማካኝነት ወደአገር ቤት እንደገባ፣ ህጋዊነቱ መረጋገጡንና ምዝገባ ማከናወኑን ጨምሮ ምልከታ ማድረግና ማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።
መተግበሪያውን ለመጠቀምም ከፕሌይ ስቶር ላይ አይ ቬሪፋይ(I-VERIFY)የተሰኘ መተግበሪያን በማውረድና መድኃኒቱን ለመተግበሪያው ስካን በማድረግ መረጃዎቹን ማወቅ ይቻላል ነው ያሉት።
መድሃኒቱ አስፈላጊውንና ትክክለኛውን መረጃ ካላሳየና አጠራጣሪ ነገር ካለ በመተግበሪያው አማካኝነት ጥቆማ ማድረግ የሚቻልበት አሰራር እንደተዘረጋም ገልጸዋል።
ይህ መተግበሪያ የመጀመሪያ ምዕራፍ መሆኑንና በቀጣይም በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት መድኃኒቶች ልዩ መለያ ቁጥር ኖሯቸው ከአምራች እስከ ተጠቃሚው መከታተል የሚያስችል አሰራር እንደሚታከልበት ጠቁመዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ በበኩላቸው መተግበሪያው በህብረተሰቡ ዘንድ በተደጋጋሚ የሚነሱ የመድሃኒት ብራንድና የፈዋሽነት ደረጃን በተመለከተ ምላሽ የሚሰጥ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በኮንትሮባንድ የሚገቡ መድሃኒቶች እያደረሱ ያለውን የጤና ጉዳት ለማስቀረትም ያግዛል ነው ያሉት።
ተንቀሳቃሽ ስልክ የያዘ ማንኛውም ግለሰብ መተግበሪያውን በቀላሉ እንዲጠቀም ተደርጎ መሰራቱ አስተዋጾውን የጎላ እንደሚያደርገው አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት ህጋዊነታቸውና ደህንነታቸው ያልተረጋገጡ መድሃኒቶች በስፋት መሰራጨታቸውን ተከትሎ ህብረተሰቡን ለመድሃኒት መላመድ ችግር እየተዳረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
መተግበሪያው በዚህና ተያያዥ ችግር ምክንያት የሚፈጠሩ ስጋቶችን ያስቀራል ብለዋል።