ባለፉት 20 ቀናት 993 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት 20 ቀናት 993 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6/(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ባከናወነቻቸው ተግባራት 993 ኢትዮጵያዊያን ከተለያዩ አገራት ወደ አገርቤት መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባለፉት 20 ቀናት የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በተሰራው ስራ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱት ዜጎች መካከል 953ቱ ከሳኡዲ አረቢያ፣ 35 ከጂቢቲ እና አምስት ከታኒዛኒያ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሂደቱም ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ያደረጉት የስራ ጉብኝትም የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
በአገር ውስጥ ለሚኖሩ ለተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እና የዲፕሎማሲ አባላትም የኢትዮጵያ ምርጫ የተራዘመበትን ጉዳይ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል የተካሄደውን ህገ-ወጥ ምርጫ አስመልክቶ ስላሳለፈው ውሳኔ ገለጻ መደረጉንም አምባሳደር ዲና ገልጸዋል፡፡
በ37ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራአስፈፃሚዎች ስብሰባ ላይም ኢትዮጵያ ጥቅሟን በሚያስጠብቅ እና በማይነካ መልኩ መሳተፏን አውስተዋል፡፡
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተወጣጣ የልዑካን ቡድንም በሱዳን በመገኘት በጎርፍ ለተጎዱ ዜጎች ባደረገው ድጋፍ በሱዳናዊያን በኩል መልካም ስሜትን የፈጠረ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ረገድም ጀርመን እና ህንድን ከመሳሰሉ አገራት ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር ተሳትፎና ውይይቶች እንደተደረጉ ተናግረዋል።
ባለፉት 20 ቀናት ዘጠኝ የውጭ አገራት አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤያቸውን አቅርበዋል ያሉት ቃል አቀባዩ ሁለቱ ከአፍሪካ ማለትም ከሴራሊዮን እና ካሜሩን ሲሆኑ ቀሪዎቹ ከአውሮፓ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
አምባሳደሩ አክለውም በ75ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ እንደመስራችነቷ ለባለብዙ ወገኖች መድረክ ያላትን ቁርጠኝነት ማሳየቷንም ነው በሳምንታዊ መግለጫቸው ያሳወቁት፡፡