ቀጥታ፡

ፈረንሳይ፣ ስፔንና ፖርቹጋል ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴግድብ ከ20 ሺህ ዩሮ በላይ ተሰበሰበ

 አዲስ  አበባ ጥቅምት  6/2013 (ኢዜአ) ባለፉት ሁለት ወራት ፈረንሳይ፣ ስፔንና ፖርቹጋል ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከ20 ሺህ ዩሮ በላይ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሰብሰቡ ተገለጸ።

በሶስቱ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ለሚከናወኑ ስራዎች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑም ተጠቁሟል። 

በሶስቱ አገራት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ባለፉት ሁለት ወራት በአገራቱ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከ20 ሺህ ዩሮ በላይ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰብሰቡን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም መሻሻል ማሳየቱና ባለፈው ዓመት የግድቡ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ በአገራቱ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሯል ብለዋል።

በዚህ መሰረት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተቋቁሞ የሀብት ማሰባሰሰቡን ስራ እያከናወነ መሆኑን ነው አምባሳደር ሄኖክ ያስረዱት።

በአውሮፓ አገራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን አስመልክቶ በተጣሉ ገደቦች ምክንያት የሀብት ማሳባሰቡ ስራ በከፊል በአካልና በበይነ-መረብ በሚካሄዱ መድረኮች እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት በፈረንሳይ፣ ስፔንና ፖርቹጋል ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ 40 ሺህ ዩሮ ለማሰበሳብ እቅድ መያዙን ተናግረዋል።

ይሁንና አሁን እየተሰበሰበ ያለውን ገንዘብ ከግምት ውስጥ በማስገባት እቅዱን የመከለስ ተግባር እንደሚከናወን ነው አምባሳደር ሄኖክ ያመለከቱት።

ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ በሶስቱ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ያላትን አቋም የማስረዳት(አድቮኬሲ) ስራ እየሰሩ ነው ብለዋል።

በተለይም በፈረንሳይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲና በአገሪቷ በተለያዩ የትምህርት ጥናት ተቋማት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለፈረንሳይ መንግስትና በአገሪቷ ለሚገኙ ተቋማት በግድቡ ዙሪያ ገለጻ እያደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።

በተጨማሪም በሶስቱ አገራት ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስለ ግድቡ ግንዛቤያቸው እንዲያድግ መድረኮችን በመፍጠር ገለጻ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በሶስቱ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘብና በእውቀት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጊዜ አንስቶ በፈረንሳይ፣ ስፔንና ፖርቹጋል የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወረርሽኙን ለመከላከል ለሚያስፈልጉ የህክምና ቁሳቁሶችና መሳሪያዎች የሚውል ከ117 ሺህ ዩሮ በላይ የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማድረጋቸውንም ነው አምባሳደር ሄኖክ የገለጹት።

በአገራቱ የሚኖሩ ዜጎች 55 ሺህ ዩሮ በገንዘብ ከ62 ሺህ ዩሮ በላይ በአይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

በገንዘብና በአይነት በተደረገው ድጋፍ የተገኙ የህክምና መሳሪያዎች ቁሳቁሶች ሁሉም ወደ ኢትዮጵያ መጓጓዛቸውንና 37 ሺህ ዩሮ የሚገመት የህክምና ግብአቶች ከቀናት በፊት ኢትዮጵያ መግባቱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የህክምና ግብአቶቹን በነጻ በማጓጓዝ እንዲሁም የኢትዮ-ፈረንሳይ ወዳጅነት ማህበር እና የኢትዮ-ስዊዝ ማህበር የድጋፍ ማሰባሰቡን በማስተባበር እያከናወኑት ላለው ስራ አምባሳደር ሄኖክ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚሰሩ ስራዎች የሚደረገው ድጋፍ ቀጣይነት ያለው መሆኑንም አመልክተዋል።

የዲያስፖራው ማህበረሰብ በ2013 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ24 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በተጨማሪም በሩብ ዓመቱ ለግድቡ ግንባታ ከ17 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱ ተገልጿል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ከገባ ጊዜ አንስቶ የዲያስፖራው ማህበረሰብ ወረርሽኙን ለመከላከል ለሚያስፈልጉ የህክምና ቁሳቁስና መሳሪያዎች ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በገንዘብና በአይነት ድጋፍ ማድረጉን ኤጀንሲው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም