ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ የአደጋ ስጋት አመራር ስራን በዕውቀትና ቴክኖሎጅ ለመምራት የሚያስችል ስትራቴጅክ

አዳማ ጥቅምት 06/2013 (ኢዜአ) የመዲናይቱን ልማትና ዕድገት ታሳቢ ያደረገ የአደጋ ስጋት አመራር ስትራቴጅክ ዕቅድ ማዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በሩብ አመቱ ዕቅድ አፈፃፀምና በቀጣይ አምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ለማዳበር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ አዳማ ከተማ ተጀምሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሰለሞን ፍሰሃ በወቅቱ እንደገለፁት የከተማዋን ልማትና ዕድገት የሚመጥን ተቋም መገንባት አስፈልጓል።

የአደጋ ስጋት ቅነሳና አመራር ስራዎችን በዕውቀትና ቴክኖሎጅ ለመምራት የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

"አሁን ላይ የከተማዋን ዕድገት የሚመጥን የቴክኖሎጂና የሀብት ዝግጅት የለም" ያሉት ኮሚሽነሩ ዕቅዱ ተቋሙን በቴክኖሎጂ ለመገንባትና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል ።

"በቀጣይ አምስት ዓመት ተቋሙን በሄሊኮፕተርና ጀልባዎች ጨምሮ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ  በማደራጀት ስራዎችን ለመምራት የሚያስችል አቅም ይገነባል" ብለዋል።

በኮሚሽኑ የአደጋ መከላከልና መቆጣጠር ማሰልጠኛ ማዕከል ኃላፊ ዶክተር አማን አሰፋ  በኮሚሽኑ የተዘጋጀውን እቅድ ለውይይት አቅርበዋል ።

ዶክተር አማን በወቅቱ እንዳሉት በተለይ የስልጠና ማዕከሉን በግብዓትና ቴክኖሎጂ ማደራጀት ለዕቅዱ ስኬት ወሳኝ ነው።

"ተቋሙ በቂ ዕውቀት ያለው ከቴክኖሎጂ ጋር የተዋሃደ የሰው ኃይል መፍጠር ይገባዋል" ብለዋል።

እቅዱ ስጋትን ታሳቢ ያደረገ አሰራር መዘርጋት፣ የውስጥ አቅምን ማጠናከርና አሁን የሚታዩ ክፍተቶችን መሙላት የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።።

የተቋሙን የአገልግሎት ተደራሽነት ማሳደግ፣ ውጤታማ የሆነ የአደጋ ቅነሳ ስራን ማከናወን፣ የህብረተሰን የአደጋ ክህሎትና ግንዛቤ ማጎልበትና ተሳታፊ ማድረግ የዕቅዱ አንድ ግብ  መሆኑን ጠቅሰዋል ።

እቅዱ አዲስ አበባ ከተማና አካባቢውን ከአደጋ የፀዳ ለማድረግ መሰረት የሚጣልበት እንደሆነ ዶክተር አማን አስታውቀዋል።

ለሶስት ቀን በሚቆየው መድረክ ላይ በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራሮችና ሙያተኞች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም