ቀጥታ፡

ለ"ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት ዳያስፖራው ከ10 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6/2013 (ኢዜአ) ለ"ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት ዳያስፖራው እስካሁን ከ10 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአማራ ክልል ጎርጎራ፣ በኦሮሚያ ክልል ወንጪና በደቡብ ክልል ኮይሻ የሚገኙ አካባቢዎችን ለማልማት በነሐሴ 2012 ዓ.ም የ“ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክትን ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።

ፕሮጀክቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ በተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ሥር የዳያስፖራውን ተሳትፎ የሚያስተባበር ንዑስ ኮሚቴ ተቋቁመው ወደ ሥራ መግባቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ለኢዜአ ገልጸዋል።

እስካሁንም ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ 10 ሚሊዮን 484 ሺህ 986 ብር ለ"ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት ድጋፍ ማድረጉን ይፋ አድርገዋል።

በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ካደረጉት መካከል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች እንዲሁም አምባሳደሮችና ሚሲዮኖች የወር ደመወዛቸውን ለ"ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት መለገሳቸውንና ይሄም ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚያስተባብሩ ድርጅቶችም የ"ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክትን ጨምሮ በሌሎች አገራዊ የልማት ሥራዎች ላይ ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው አመልክተዋል።

በ2013 ዓ.ም ኤጀንሲው ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ ለ"ገበታ ለሀገር" ፕሮጀክት 50 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱንም ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ለፕሮጀክቱና ለሌሎች አገራዊ የልማት ሥራዎች የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

በ2013 በጀት ዓመት የሐምሌና ነሐሴ ወራት ብቻ ዳያስፖራው 420 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ (ሬሚታንስ) ወደ አገር ውስጥ መላኩን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሁለት ወራት 825 ዳያስፖራዎች የባንክ ሂሳብ ቁጥር በመክፈት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ማስቀመጣቸውን ጠቁመዋል።

ኤጀንሲው እንደገለጸው በ2013 በጀት ዓመት ዳያስፖራው ወደ አገር ውስጥ ከሚልከው ገንዘብ (ሬሚታንስ) 4 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም