በአዲስ አበባ ከ2 ሺህ 300 በላይ ተገጣጣሚ የመማሪያ ክፍሎች ሊገነቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከ2 ሺህ 300 በላይ ተገጣጣሚ የመማሪያ ክፍሎች ሊገነቡ ነው
አዲስ አበባ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ/ም (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ለ2013 የትምህርት ዘመን ከ2 ሺህ 300 በላይ ተገጣጣሚ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ሊገነቡ መሆኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
በከተማዋ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እስካሁን 400 ሺህ ተማሪዎችን መመዝገባቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በኢትዮጵያ ከ30 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በትምህርት ላይ ቢሆኑም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ከ7 ወራት በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።
ይሁን እንጂ ትምህርት ቤቶችን ዘግቶ ማቆየት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እያመዘነ በመሆኑ አስፈላጊውን የጥንቃቄ በማድረግ ዳግም ተከፍተው ስራ እንዲጀምሩ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ትምህረት ቢሮ እንዳስታወቀው በመዲናዋ ትምህርት ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው።
የኮሮናቫይረስን የመከላከል አማራጮችን በመከተል የመማር ማስተማር ስራውን መጀመር አስፈላጊ መሆኑንም የዘርፉ ተዋንያን ይናገራሉ።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አዲሱ ሻንቆ በበኩላቸው ''ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ በተማሪዎች ዘንድ በወላጆች ዘንድ በመምህራን ዘንድ ትምህርት ቤት በሚሰሩ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ዘንድ ቤት በሚቀመጡበት ጊዜ የሚደርሰው ማህበራዊ፣የስነ-ልቦና ጫናዎች አሉ።'' ብለዋል፡፡
ለልጆች ትምህርት ቤት መዋል ራሳቸውን የሚያዝናኑበት ትልቅ ስፍራ ነው ከመማር ማስተማር ሂደት በተጨማሪ ያሉት ደግሞ አቶ አየለ ሳህሌ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ዓለም አቀፉ ጤና ድርጅትና ጤና ሚኒስቴር ባስቀመጡት ምክር ሃሳብ መሰረት ኮቪድን መከላከል ማዕከል ባደረገ መልኩ በመላ አገሪቷ ትምህርት ለማስጀመር መወሰኑ ይታወቃል።
በመሆኑም በአዲስ አበባ ትምህርት ለመጀመር ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አዲሱ ሻንቆ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በዝግጅቱ የመማሪያ ክፍሎችን የማፅዳት ሥራ እየተከናወነ ሲሆን ከ2 ሺህ 300 በላይ ተገጣጣሚ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችም ይገነባሉ ብለዋል።
ቀደም ብሎ ትምህርት በመቋረጡ ትምህርት ቤቶች ለተለያዩ ተግባራት በማዋላቸው ለመማር ማስተማሩ ስራ ምቹ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ እስካሁን ከ400 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርት ለመጀመር የተመዘገቡ ሲሆን የተጠቀሰውን ቁጥር ያህል ደግሞ ይመዘገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ወላጆችም ልጆቻቸውን በማስመዝገብ ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ አቶ አዲሱ አሳስበዋል።
የኒው ኤራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ወይዘሮ ሀመረ ታደሰም ተማሪዎች በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መመዝገብ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
ትምህርት ሲጀመር በየትምህርት ቤቱ በአካባቢ ጥበቃና በመጀመሪያ ህክምና ላይ የተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች በኮንትራት እንዲሰሩ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በዚሁ መሰረት የባለሙያዎች ቅጥር እየተከናወነ መሆኑም ታውቋል።