የኤርትራው ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት - ኢዜአ አማርኛ
የኤርትራው ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት
አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2010 የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች ግንኙነት የተመሰረተው በጉርብትና ብቻ አይደለም። ተመሳሳይ ባህልና ቋንቋ ያላቸው በመሆናቸውም ብቻ አይደለም። የአገሮቹ ህዝቦች ከዚህም በላይ ተዋልደው በደም ጭምር የተቆራኙ ስጋ ዘመድ ህዝቦች ናቸው። የታሪክ አጋጣሚ ሆነና ይህ በደም የተሳሰረው ወንድምና እህት ህዝብ ተራርቆ ለሁለት አስርት ዓመት ቆየ። የመገናኛ ስልቶች ሁሉ ተከረቸሙ። መንገዶች ተዘጉ፣ የስልክ መስመር ገመዶች ተበጠሱ፣ የአየርም ሆነ የየብስ ግንኙነት ተቋረጠ። በአየር በረራ ክልሎቻቸው ላይ ሳይቀር የተናጠል ክልከላ ጣሉ። ይህ በደም የተሳሰረው የህዝቦቹ መስተጋብር ፍፁም ሊባል በሚችል መጠን ነበር ተቆልፎ ሁለት አስርት ዓመታት እንደዋዛ የነጎዱት። ጦርነትም ሆነ ሰላም አለ ለማለት በሚያዳግት መልኩ የቆየው ግንኙነት በተለይ በሁለቱ አገሮች አዋሳኝ ድንበሮች አካባቢ ያሉት ህዝቦችን ህይወት የሰቀቀን አድርጎት እንደነበር በዙዎች ይናገራሉ። ከዚህም በላይ ወላጅና ልጆችን፣ ወንድም እና እህትን ጨምሮ ተነጣጥለው የሚኖሩ በርካታ በደም የተሳሰሩ ቤተሰቦችን ስቃይንም ቤቱ ይቁጠረው። እንደቀልድ የነጎደው ይህ ሁለት አስርት ዓመት በቀድሞው መልካም ግንኙነት ውስጥ ያለፈ ቢሆን ኖሮ ምን ያህል አገሮቹ ተጠቃሚ በሆኑበት እንደነበር የሚገምቱትም አያሌዎች ናቸው። ዛሬም አልረፈደም። አገሮቹ ማንም ባልጠበቀውና ባልገመተው መንገድ ግንኙነታቸውን ወደቀድሞው ለመመለስ የሚያመረቃ ተግባር ጀምረዋል። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት በኤርትራ ያደረጉትን ድንገተኛ ጉብኝት ተከትሎ በሁለቱ መካከል የቆየው ግጭት ማብቃቱን የሚያበስር መግለጫ ከወደአስመራ ተሰምቷል። ከዚህ ቀደም ፍጹም ተቋርጦ የቆየው የህዝቦች ግንኙነት እንዲቀጥል ሁሉም ተዘግተው የነበሩት በሮች ተከፍተዋል። ለሁለት አስርት ዓመታት ተራርቀው የቆዩ ቤተሰቦች በስልክ ገመድ ተገናኝተው ናፍቆታቸውን ተወጥተዋል። ሰሞኑን ደግሞ የአየርም ሆነ የየብሰ ግንኙነቱ የሚከፈት መሆኑም ተበስሯል። ይህ ብስራት ተሰምቶ በሳምንቱ ትናንት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከ22 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያቸው የሆነውን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ትናንት አዲስ አበባ ገብተዋል። የአዲስ አበባና አካባቢው ህዝብም ለማንም ሌላ አገር መሪ ተደርጎ የማያውቅ የሚመስለውን ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስም ሁለቱ አገሮች በደም የተሳሰሩ መሆናቸው ገለፁ። "የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ ሁለት ህዝቦች ናቸው ብሎ የሚናገር እውነታውን የማያውቅ ብቻ ነው" ሲሉ በብሔራዊ ቤተ መንግስት ለእርሳቸው ክብር በተዘጋጀው የምሳ ግዣ ላይ ተናገሩ። “አሁን በሁለቱም አገሮች የተፈጠረውን ሰላም ህዝቡ በደንብ ገልጾታል፤ እኛ ከህዝብ በኋላ ነን ይህ ደግሞ ለሁለቱም አገሮች ኩራት ነው፤ ከዚህ የበለጠ ሀብት የለም፤ ይህንን ሳያዩ ላለፉት በጣም እናዝናለን፣ እኛ ግን ይህንን በማየታችን በጣም ዕድለኞች ነን፤ ወደፊት አብረን እንራመዳለን ሁለቱን ህዝቦች እንክሳለን'' ሲሉም ፀፀትና ተስፋቸውን ገለፁ። ከምሳ ግብዣው በኋላም ወደሀዋሳ ከተማ በማምራት እዚያ የሚገኘውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ጎብኝተዋል። ፕሬዚዳንቱ ሀዋሳ ሲደርሱ የተደረገላቸው አቀባበልም ልዩ ነበር። የክልል መሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ ስጦታዎችን በማበርከት አክብሮታቸውን ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት አገሮቹ አዲስ የግንኙነት ምእራፍ ጀምረዋል። ይህንን መልካም ዜና ለማብሰርና ምስጋናም ለማቅረብ አንድ ዝግጅት በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ በመካሄድ ላይ ነው። በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ጭምር በተሳሰሩት የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች መካከል ላለፉት 20 ዓመታት ሰፍኖ የቆየውን ‘ሞት አልባ ጦርነት' ከፍፃሜ ያደረሰውን ይህንን አዲሰ የግንኙነት ምእራፍ ለማብሰር በተዘጋጀት ልዩ መርሃ ግብር ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ታድመዋል። በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ በተካሄደው በዚህ መርሃ ግብር ላይ ከ25 ሺህ በላይ የሚሆን ህዝብ ተገኝቷል። መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተፈጠረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከርና ወደላቀ ደረጃ ለማሻገር ትልቅ ሚና እንዳለው ተመልክቷል።