ኢትዮጵያዊያን የቀደመ የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶቻቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን የቀደመ የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶቻቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ
አዲስ አበባ ጥቅምት 5/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ለሰላም ሲሉ የቀደመ የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶቻቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ። ሰላም የአንድ አገር ሁሉን አቀፍ ህልውና በመሆኑ ዜጎች ሊጠብቁት ይገባልም ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማትና የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤዎች አስተባባሪነት "ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ ሐሳብ የተለያዩ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የአገር ሽማግሌዎች፣ የኃማኖት አባቶች፣ የጸጥታና ፍትህ አካላት እንዲሁም ምሁራን ተሳትፈዋል።
በምክክር መድረኩ ወቅት እንደተገለጸው ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የኢትዮጵዊያን የቀደመ የአብሮነትና የመከባበር እሴት መቀጠል እንዳለበት ተመላክቷል።
የአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እና የአዲስ አበባ የሰላም ምክር ቤት ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደ-ሃና እንደገለጹት ሰላም የሰው ልጆች የግላዊና ማህበራዊ ደህንነት መሰረት ነው።
ዛሬን ኖሮ ነገን ለማየት ሰላም የእድግት፣ የድስታ፣ የልማት እና የአገር የህልውና ምሰሶ በመሆኑ በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን የቀደመ የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶቻቸውን የማስቀጠል ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ለሰላም እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት የሁሉም ዜጋ ትብበርና ሃላፊነት ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሰላም ትብብርና ቅንጅትን የሚጠይቅ ጉዳይ በመሆኑ የኃይማኖት አባቶች ወጣቶችን በማስተማርና በማስተባባር ስለ ሰላምና ልማት በጋራ የመስራት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ፕሮፌሰር ጣሰው ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ የሰላም ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢዋ አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ በበኩሏ ሰላም ለሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አስፈላጊና ውድ ሃብት መሆኑን ተናግራለች፡፡
የምክክር መድረኩ ዋና አዘጋጅና አስተባባሪ ዶክተር ወሰን ባዩህ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚስተዋሉ የሰላም መደፍረሶችና ግጭቶች አገሪቱ ቀደም ሲል ትታወቅባቸው የነበሩ የሰላምና የመቻቻል እሴቶች እየተሸረሸሩ በመምጣታቸው መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑም ሰላም የሁሉንም ዜጋ ስራና ሃላፊነት የሚጠይቅ በመሆኑ በጋራ መቆም አለበን ብለዋል።
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ አባል ዶክተር ኤርሚያስ ማሞ፤ የኃይማኖት ጉባዔው ወጣቶች ሰላም ወዳድ፣ በስነ-ምግባር የታነጹ እና የመቻቻል ተምሳሌት እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በርካታ እድገቶች እንደተመዘገቡት ሁሉ ከማንነት፣ ወሰንና እራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን ሁሉም ወገን የአንዱን ሃሳብ ሳይጥል በጋራ በመሰባሰብ ሰላማዊ በመሆነ መንገድ ችግሮችን መፍታት አለበት ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ናቸው
በምክክር መድረኩ ላይ በዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ በኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት እና በትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያዎች የተሰናዱ ጥናታዊ ጹህፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡