በህዳሴ ግድብና ሌሎች ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንቆማለን--የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
በህዳሴ ግድብና ሌሎች ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንቆማለን--የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 5/2013 (ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ሌሎች ወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራና በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ በሀገር ወስጥም በውጭም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ድጋፋቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ሃላፊዎች እንደሚሉትም ፖለቲካዊ እሳቤያቸው ቢለያይም በህዳሴ ግድብና ሌሎች ብሄራዊ ጥቅሞች ላይ ግን ልዩነት የለም።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ እንዳሉት በወሳኝ የጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መቆም እንጂ ልዩነት አይኖርም ።
ከምንም በላይ ለሀገራዊ ጥቅምና ብሄራዊ ደህንነት መስራት ከዜጎች የሚጠበቅና የሰለጠነ አስተሳሰብ መሆኑንም አቶ የሺዋስ ጠቅሰዋል።
የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የአጠቃቀምና ኤሌክትሪክ የማመንጨት ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱና የህዝቦቿ የነጻነትና ሉአላዊነት መገለጫ በመሆኑ ለስኬቱ በጋራ እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብም በህዳሴ ግድብ ዙሪያ እያደረገ ያለው ትብብር የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው ሁሉም በጋራ በመቆም አንድነቱን አሳይቷል ብለዋል።
የግድቡ ጉዳይ ከግለሰብም ሆነ ከፓርቲ በላይ የሀገር ጉዳይ በመሆኑ ፓርቲያቸው ለግድቡ ስኬት የድርሻውን የሚወጣ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የሱፍ ኢብራሂም በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም ብለዋል።
ፓርቲያቸው ከዚህ ቀደም በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ለመንግስት በባለሙያዎች የተጠና ጠቃሚ ሰነድ አዘጋጅቶ የሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም አንድነቱን ያሳየበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሆኑም ፓርቲው በግድቡ ዙሪያ ማገዝ በሚገባው ጉዳይ ላይ እገዛ ማድረጉን እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) የፖለቲካ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ጊደና መድህንም የህዳሴ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኩራት በመሆኑ ለስኬቱ እንሰራለን ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ለታለመለት አላማ እንደሚውልም አንጠራጠርም ብለዋል አቶ ጊደና።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታገል ቀኑብህ ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በዚህም ዜጎች ልማቱን ለማስቀጠል ብሎም የሀገሪቱና የህዝቦቿ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ እንዲያድግ በሚደረገው ጥረት አሻራቸውን እያሳረፉ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ህዝቡ አንድነትና ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አቶ ታገል ጥሪ አቅርበዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሁለት ወራት ብቻ ከህብረተሰቡ ከቦንድና ከስጦታ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘት ተችሏል።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁናዊ አፈፃፀም 76 በመቶ መድረሱ ይታወቃል።