የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የዳክዬ አረምን ለእንስሳት መኖነት እንዲውል ማድረጉን አስታወቀ

96
አምቦ ሀምሌ 8/2010 የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የዳክዬ አረምን በምርምር ለእንስሳት መኖ  አገልግሎት እንዲውል ማድረጉን አስታወቀ ። በዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ብዙነሽ ሚደግሣ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ስታንድ ፎር ቨልነረብል ከተባለ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ባለፉት ሶስት ዓመታት በዳክዬ አረም ላይ ያካሔደው ምርምር ውጤታማ ሆኗል ። የዳክዬ አረም ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት ያለውና ለዶሮ ፣ ለወተት ላሞችና ለዓሳ እርባታ በመኖነት በማገልገል የላቀ ጠቀሜታ የሚሰጥ መሆኑን በምርምር እንደተረጋገጠ ዶክተር ብዙነሽ ተናግረዋል ። የምርምር ውጤቱ ሴቶችን ማዕከል አድርጎ ወደ ተጠቃሚው ለማድረስ እየተሰራ ነው፡፡ መሆኑንም አስረድተዋል ። የዳክዬ አረምን ለመኖ አገልግሎት በማዋል ለእንስሳት መኖ ይወጣ የነበረው ወጪ 60 በመቶ መቀነስ እንደሚቻል በተግባር ተረጋግጧል ። ተጠቃሚዎች አረሙን ወደ እንስሳት መኖነት የሚለውጡበት የአዘገጃጀት ዜዴ በተመለከተም በማህበር ለተደራጁ ሴቶች ስልጠና መሰጠቱን ከዶክተር ብዙነሽ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ። በዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ጫላ መረራ በበኩላቸው የምርምር ውጤቱ ወደ ተጠቃሚዎች ለማድረስ በአራት ወረዳዎች የሚኖሩ 1ሺህ 200 ሴቶች በማህበር ተደራጅተው በቂ ስልጠና እንዲያገኙ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ስታንድ ፎር ቨልነረብል የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ዳይሬክተር  አቶ ምስጋናው ኢቲቻ እንደገለፁት ደግሞ ድርጅታቸው የዩኒቨርሲቲው ምርምር በገንዘብ ከመደገፍ ባሻገር በማህበር ለተደረጁ ሴቶች መኖውን ተጠቅመው ውጤታማ እንዲሆኑ ዶሮዎችን ገዝቶ አከፋፍሏል ። በቀጣይነትም የምርምር ውጤቱ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች በማዳረስ ና ሴቶችና ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ  ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል ። "ድርጅቱ ሴቶች መኖውን ከዶሮ እርባታ ባሻገር ለወተት ላሞች ቀለብ እንዲጠቀሙበት ለማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል "ብለዋል ። በአምቦ ወረዳ የሜጢ ከተማ ነዋሪና የምርምር ውጤቱ ተጠቃሚ ወይዘሮ አዳኑ ባይሣ በሰጡት አስተያየት 12 ሆነው በማህበር በመደራጀት ከድርጅቱ ያገኟቸውን  200 ዶሮዎች የዳክዬ አረምን አዘጋጅተው በመቀለብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም ልጆቻቸውን እንቁላል በመመገብ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሰውነታቸው ላይ አካላዊ መሻሻል መታየት መጀመሩንም ወይዘሮዋ ገልፀዋል፡፡ በማህበር ተደራጅተው ከሚያረቡት ዶሮዎች በሚገኝ ጥቅም የልጆቿቸውን የምግብ ፍላጎት ማሟላት እንደቻሉ የተናገሩት ደግሞ በኤጀርሳ ለፎ ወረዳ የኦሎንኮሚ ከተማ ነዋሪና የምርምር ውጤቱ ተጠቃሚ ወይዘሮ አልማዝ ኢረና ናቸው፡፡ ተደራጅተው ዶሮ በማርባት ከሚያገኙት ገንዘብ በመቆጠብ በማህበራቸው ስም 7ሺህ ብር ባንክ መቆጠባቸውን ጠቅሰው  በምርምር የተገኘው የዳክዬ አረም ዶሮዎቹን ምርታማና ጤናማ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል ። የምርምር ውጤቱ በኤጀርስ ለፎ ፣ በአምቦ ፣ በጨሊያና በባኮ ቲቤ ወረዳዎች የተዳረሰ ሲሆን በቅርቡ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም