ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ለህዝባዊ አንድነትና የኢኮኖሚ ግንባታ ያለውን ሚና ለማሳደግ እሰራለሁ-- ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አረጋዊ

አዲስ አበባ ጥቅምት 5/2013 (ኢዜአ) ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግንባታና ህዝባዊ አንድነት ያለውን ሚና ለማሳደግ እንደሚሰሩ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር በመሆን አዲስ የተሾሙት ዶክተር አረጋዊ በርሄ ተናገሩ።

ዋና ዳይሬክተሩ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገትና የአንድነት መጠናከር አይነተኛ ሚና አለው።

በመሆኑም ለዚህ ታላቅ የህዝብ ፕሮጀክት ግንባታ ለተሰጠኝ ሃላፊነት ደስተኛ ነኝ ያሉት ዶክተር አረጋዊ ስራውን በብቃት ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ እንዲበቃ የሁሉም ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታልም ነው ያሉት።

በተለይም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው ልማት ጉልህ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው ሁለንተናዊ ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በውጭ ያለውን አቅም በማቀናጀት እስካሁን በቂ ስራ አለመከናወኑን ጠቅሰው በቀጣይ ግን ትኩረት ሊደረግበት ይገባል ብለዋል።

በሀገር ውስጥ በሚፈጠሩ የተለያዩ የፖለቲካ ልዩነቶች ምክንያት በውጭም ይሁን በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ሳይከፋፈሉ ለሀገራዊ ልማትና እድገት በጋራ መቆም ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት።

"በውጭ ሀገር ከ30 አመትታት በላይ ስለኖርኩ የዲያስፖራውን ስነ ልቦና አውቀዋለሁ" ያሉት ዶክተር አረጋዊ ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ ትልቅ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ አይነት ፕሮጀክቶች ላይ የሚያደርገው ድጋፍና ተሳትፎ እንዲቀጥል ለማስቻል የድርሻቸውን ሃላፊነት እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁናዊ አፈፃፀም 76 በመቶ መድረሱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም