ሁሉም አካላት እጅን የመታጠብ ልምድ ለማጎልበት እንዲረባረቡ የጤና ሚኒስትሯ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5/2013(ኢዜአ) ከንጽህና ጉድለት የሚመጡ በሽታዎችን ለመከላከል እጅ አዘውትሮ መታጠብ እንዲጎለብት ሁሉም አካላት እንዲረባረቡ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አሳሰቡ።

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ እጅ የመታጠብ ቀን "ሕይወትን ለማዳን እጄን በደንብ እታጠባለሁ!" በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው።   

ሚኒስትሯ ቀኑን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳስገነዘቡት የእጅ መታጠብ ባህል እንዲጎለብት መሥራት ይገባል ።  

በኢትዮጵያ በወሳኝ ሁነቶች ላይ እጅ የመታጠብ ምጣኔው ከአምስት በመቶ በታች መሆኑን ገልጸው፣ ይህም 30 በመቶ ለሚሆነው የበሽታ መንስኤ ሆኗል ብለዋል።

በአገሪቱ እጅ ባለመታጠብ 25 በመቶ የሚሆኑ ከአምስት ዓመት በታች ሕፃናት እንደሚሞቱ ገልጸዋል። 50 በመቶ  ሕፃናት የሚቀነጭሩትም በዚሁ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን 80 በመቶ የሚሆኑት ጀርሞች ከሰው ወደ ሰው እንዲተላለፉና የበርካታ ኢንፌክሽን ምክንያቶችም የእጅ ንጽህና ጉድለት መሆኑን  ሚኒስትሯ ተናግረዋል።    

ስለሆነም እጅን በደንብ በመታጠብ የበሽታዎችን ስርጭት መቀነስ እንደሚገባ ገልጸው፣ ለዚህም ደግሞ ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ ነው ዶክተር ሊያ ያሳሰቡት።

ኮቪድ-19 ያመጣው ጫና እንዳለ ሆኖ፤ በተለይም እጅን የመታጠብ ልምድ እንዲጎለብት ማድረጉን ጠቁመው ይህም በቀጣይ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል። 

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በበኩላቸው ትምህርትን ውጤታማ ከሚያደርጉ  የመሠረተ-ልማት አቅርቦት ውስጥ ንጹህ ውሃና የንጹህና አገልግሎት አንዱ ነው።

ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ከ27 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በሚማሩባቸው የትምህርት ተቋማት መካከል የንጹህ ውሃ አቅርቦት ያላቸው 32 በመቶው ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህንን ሁኔታ ለመቀየርና በተለይም ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከግምት በመውሰድ የትምህርት ተቋማት የውኃ አቅርቦት ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ነጋሽ ዋጌሾ በተወካያቸው ባስተላለፉት መልዕክት ሚኒስቴሩ የንጹህ ውሃና የንጽህና አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት እየሰራ ነው።

በተለይም በዋሽ መርኃ ግብር በተሰሩ ሥራዎች ውጤቶች ቢኖሩም፤ አሁንም በርካታ ሰዎች በውሃ እጥረት ምክንያት ለተለያዩ በሽታዎች እየተጋለጡ መሆኑን ተናግረዋል።

መርኃ ግብሩን በማጠናከር በተለይም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከግምት ያስገባ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም