ኮቪድ-19ን የመከላከል እርምጃዎች የሴቶችና ሕፃናትን የጤና መብቶች ታሳቢ እንዲያደርግ ኢሰመኮ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ኮቪድ-19ን የመከላከል እርምጃዎች የሴቶችና ሕፃናትን የጤና መብቶች ታሳቢ እንዲያደርግ ኢሰመኮ አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5/2013(ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚወሰዱ እርምጃዎች የሴቶችና ሕፃናትን የጤና መብቶች ታሳቢ ማድረግ ይኖርበታል ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስገነዘበ።
ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚወሰዱ እርምጃዎች በሴቶችና ሕፃናት የጤና መብቶች ላይ ጫና ማሳደሩን በዳሰሳ ጥናት ማረጋገጡን አስታውቋል።
ከሐምሌ 21 እስከ ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ፣ በሲዳማ፣ በአማራ እና ጋምቤላ ክልሎች ባካሄደው ፈጣን የዳሰሳ ጥናት ማረጋገጡን ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
በጤና ተቋማት እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶች በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችና በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት የተደነገጉ መሰረታዊ መብቶችን ከማክበርና ለሴቶችና ሕፃናት ትኩረት ከመስጠት አንጻር ክፍተት መኖሩን የዳሰሳ ውጤቱ አሳይቷል፡፡
በተወሰኑ የጤና ተቋማት በተለይ በደቡብ ክልል የነፍሰጡር እናቶች የቅድመ-ወሊድ ክትትል መቀነሱንም አሳይቷል።
ከከተማ ራቅ ባሉ ቦታዎች ለወረርሽኙ በተሰጠው ትኩረት ምክንያት ለቅድመ ወሊድ እና ድህረ ወሊድ ሕክምና የአምቡላንስ አገልግሎት ማነሱንም አመላክቷል።
በዚህም ከአጎራባች ወረዳዎች ወደ ከተማ ጤና ተቋማት የሚመጡ ወላድ ሴቶች ቁጥር ቀንሷል።
ለአብነትም በጋምቤላ ክልል በገጠር ቀበሌ የጤና ኬላዎች የስነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎት በመቋረጡ እናቶች በቤት ውስጥ ወሊድ ምክንያት ለፍተኛ የደም መፍሰስ ችግር እየተጋለጡ ነው።
የሕፃናት ጤናን በሚመለከትም በአንዳንድ ቦታዎች በዘመቻ መልክ ይሰጥ የነበረው ክትባት እንዲቋረጥ መደረጉን ጠቅሷል።
የክትባት መድሃኒቶች እጥረት፣ የኩፍኝ በሽታ ምልክቶች መበራከት፣ ከ5 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትን ለሕክምና ማምጣት ማቆምና ሌሎች ችግሮች በዳሰሳው ተለይተዋል፡፡
የኮሚሽ የሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ዋና አማካሪ ዜናዬ ታደሰ "የሴቶችና ሕፃናት የጤና መብቶች በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሊጣሱ አይገባም፣ ስለዚህም ችግሩ በቶሎ ማስተካከያ ሊደረግበት ይገባል" ብለዋል፡፡
ኢሰመኮ በመግለጫው የቅድመና ድህረ ወሊድን ጨምሮ የሴቶች የስነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ለወረርሽኙ በሚሰጥ ትኩረት ሊስተጓጎል አይገባም ብሏል።
የኩፍኝ በሽታ ምልክቶች መበራከታቸውን ከግምት በማስገባት ምላሽ እንዲሰጥና የክትባት መድኃኒት አቅርቦት እንዳይቋረጥም አስገንዝቧል።
በወረርሽኙ ምክንያት ወላጆች ሕፃናት ልጆቻቸውን ወደ ሕክምና ተቋሟት እንዲወስዱ የግንዛቤ መፍጠር ሥራ እንዲከናወንም ኮሚሽኑ አሳስቧል።