ቀጥታ፡

ለቱሉ ሞዬ እንፋሎት ኃይል ማመንጫ ልማት የፋይናንስ አቅርቦት ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5/2013(ኢዜአ) ለቱሉ ሞዬ እንፋሎት ኃይል ማመንጫ ልማት የሚውል 1 ነጥብ 55 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ አቅርቦት ተገኘ።

በኢትዮጵያ ግዙፍ የተባለውና በገለልተኛ ተቋም ለሚለማው ቱሉ ሞዬ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ልማት የሚሆነው ፋይናንስ የተገኘው ከአሜሪካ አለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን መሆኑን ሲኤጄ ኒውስ ዘግቧል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የሰጠው ፋይናንስ  50 ሜጋ ዋት ኃይል ለሚያመነጨው ቱሉ ሞዬ ፕሮጀክት የቴክኒክ ልማት የሚውል መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአገሪቱ ያለውን ያልተነካ የእንፋሎት ኃይል ለማልማት ለተጀመረው ጥረት ማሳያ የሆነውና በግሉ ዘርፍ ፈር ቀዳጅ የሆነው ፕሮጀክት የኃይል አቅርቦቱን እንደሚያሳድገው ታምኖበታል፡፡

“ኮርፖሬሽኑ የፕሮጀክቱን ዲዛይን ቅርፅ ለማስያዝ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ በቴክኒካል እገዛ ይሳተፋል" በማለት የኮርፖሬሽኑ ዋና ኤክስኪዩቲቭ ኦፊሰር አዳም ቦህለር ተናግረዋል፡፡

“ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ያልተነካውን ሃብት ለኢኮኖሚ እድገት እንዲውል ያግዛል" ሲሉም ገልጸዋል።

ቲ.ኤም ጂኦተርማል ኦፕሬሽን ፒ.ኤል.ሲ በደቡብ ምስራቅ አዲስ አበባ 100 ኪሎ ሜትር ላይ በሚገኘው በቱሉ ሞዬ ፕሮጀክት ልማት ላይ የሚሳተፍ አገር በቀል ድርጅት ነው፡፡

ፕሮጀክቱን የማልማት ስራው ሲጠናቀቅ ኮርፖሬሽኑ አፈጻጸሙን በመገምገም ለትግበራ የሚሆን ተጨማሪ ፋይናንስ እንደሚለቅ ተገልጿል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የቴክኒካል ልማት የአሜሪካ መንግስት ቀደም ብሎ የኢትዮጵያን የኃይል ዘርፍ ለመደገፍ የያዘው እቅድ አካል ነው።

ፓወር አፍሪካ፣ በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ፣ የአሜሪካ የንግድና የልማት ኤጀንሲ እና የአሜሪካ የግምጃ ቤት ቢሮ በጋራ የሚሳተፉበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም