19ኛው የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
19ኛው የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል
አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2010 በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተጀመረው የሰላም ጥረት አፍሪካዊያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው ጥበብ መፍታት እንደሚችሉ ማሳያ ነው እንደሆነ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ገለፁ። 19ኛው የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። ፕሬዘዳንቱ በስብሰባው የመክፈቻ ንግግር ላይ እንዳሉት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ላለፉት 20 አመታት የቆየው ሰላምም ሆነ ጦርነት የሌለበት ግንኙነት አብቅቶ በሀገራቱ መካከል ሰላም ለማምጣት አሁን የተጀመረው ጥረት የሚያስደሰት ነው። የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንም በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ሰላምና አንድነት ለማምጣት ብርቱ ጥረት ስታደርግ መቆየቷንም አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ሀገራት መካከል የተወሰደው እርምጃ አፍሪካውያንን በራሳቸው መንገድ ችግሮቻቸውን መፍታት የሚችሉበት ጥበብ እንዳላቸው ማሳያ ነው ሲሉም ካርዲናል ብርሃነየሱስ ገልጸዋል፡፡ ዛሬ የተጀመረው ጉባኤውም በምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ስምምነት ማምጣት በሚቻልበት ስልት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይመክራልም ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላምና አንድነት የነገሰበት ይሆን ዘንድ ቤተክርስቲያኗ በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ካርዲናል ብርሃነየሱስ ተናግረዋል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሰላም፣ የፍትህና የእርቅ ገነት እንድትሆንም ፀልየዋል። 19ኛው የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ጉባኤ “በእግዚያብሔር ላይ የተመሰረተ ሕያው ብዝሃነት ሰብዓዊ ክብርና ሰላማዊ አንድነት ለመስራቅ አፍሪካ ሀገራት” በሚል መሪ ቃል ለቀጣዮቹ ስምንት ቀናት ይካሄዳል። በጉባኤው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለምታከናውናቸው ሐዋሪያዊና ማህበራዊ ስራዎች ብዝሀነትን ማስተናገድ እንዲቻል በቀጠናው ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሁፎችም በሊቃውንት የቀርባሉ ተብሏል። ፡ በተጨማሪም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ትብብር ለመፍጠር ከሌሎች የእምነት ተቋማት፣ ከመንግስታትና ከአፍሪካ ህብረት ጋር መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ጉባኤው እንደሚመክር ታውቋል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ህብረት ዘጠኝ የምስራቅ አፍሪካ አባል ሀገራት ያሉት ሲሆን ሶማሊያና ጅቡቲ ተባባሪ አባላት ናቸው፡፡ በየአራት አመቱ አንዴ የሚካሄደውን ይህንን ጉባኤ ኢትዮጵያ ስታስተናግድ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።