ቀጥታ፡

በአፋር ክልል ከ800ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከአንበጣ መንጋ ነፃ ማድረግ ተቻለ

ሠመራ ጥቅምት 5/2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የተከሰተውን የአንበጣ መንጋን ለመከላከል በተደረገው ጥረት ከ800ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ነፃ ማድረግ መቻሉን የክልሉ አርብቶ አደር ፣ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ።
የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት በአፋር የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ  ለመቆጣጠር  እያደረጉ ያሉትን ጥረቶች  በመስክ ተመልክተዋል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አሊ ሁሴን በመስክ ምልከታው ወቅት  እንዳሉት በክልሉ  የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ከግብርና ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰሩ ቆይተዋል።

ይህም ሆኖ እየተስፋፋ በመምጣቱ በክልሉ  የተለያዩ  ወረዳዎች  ውስጥ በሰብልና የእንስሳት ግጦሽ ላይ ጉዳት ቢያደርስም የመከላከሉን ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በተለይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሂሊኮፕተር የሰው ኃይል በመታገዝ የተደረገው ቅንጅታዊ ጥረት አበረታች ውጤት ማስገኘቱንና በዚህም ከ800ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከአንበጣ መንጋው  ማጽዳት ማስቻሉን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅትም  በአማካኝ በቀን 2ሺ 400ሄክታር መሬትን ከአንበጣ  ነፃ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ አመልክተው  በዚህም ክስተት እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል።

መንጋው በክልሉ ከተከሰተባቸው 29 ወረዳዎች ውስጥ  በሰባቱ  ሙሉ በመሉ ነጻ ማድረግ መቻሉንና በቀሪዎቹ ወረዳዎችም ለመቆጣጠር ጥረቱ  መቀጠሉን አስታውቀዋል።


በቢሮው የአንበጣ  መከላከል ስራ አስተባባሪ ዶክተር አያሌው ሹመት  በበኩላቸው በክልሉ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ የተከሰተው አንበጣ የመከላከሉ ስራ በቅንጅት ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ከባድ ጉዳት ማድረሱን አውስተዋል።

በቅርቡ የግብርና ሚኒስቴር የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ተገቢውን ግብአት በመመደቡ አሁን በተሻለ ሁኔታ የመከላከሉ ስራ እንዳለ ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ እንደገለጹት  በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች  የተከሰተው የበረሃ አንበጣ  በአርሶና አርብቶ አደሩ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ  ነው።

መንግስት የአንበጣ መንጋውን ለመቆጣጠር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በተሽከርካሪ፣ ሄሊኮፕተርና የሰው ኃይል  በመታገዝ  የኬሚካል ርጭት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።


የአንበጣ መንጋው  በመንግስት ጥረት ብቻ መቆጣጠር ስለማይቻል  በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ህብረተሰቡን በማሳተፍ በባህላዊ መንገድ  መከላከልና መረጃዎችን መለዋወጥ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በክልሉ ጭፍራ ወረዳ ከፊል አርብቶ አደር አቶ ይማም መሃመድ በሰጡት አስተያየት  በተወሰነ ደረጃ አንበጣው በጤፍ ሰብላቸው  ላይ ጉዳት ቢያደርስም መንግስት ፈጥኖ በሄሊኮፍተር የታገዘ  የኬሚካል ርጭት በማድረጉ እንዲታደጋቸው ተናግረዋል።

የአዋ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሁመድ መሃመድ በበኩላቸው በአካባቢያቸው የአንበጣው ክስተት በመስፋፋቱ  በበቆሎ ሰብልና  እንደ ማንጎና ሙዝ የመሳሰሉ ቋሚ ተክሎች ላይ ጉዳት እንዳደረሰባቸው አስረድተዋል።

አሁን ላይ  መንግስት ባደረገው የኬሚካል ርጭት የአንበጣው መስፋፋት እየቀነሰ በመምጣቱ መስኖ ተጠቅመው እንደገና ለማልማት በዝግጅት ላይ እንዳሉ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በአፋር  አጎራባች በሆኑት  አማራና ትግራይ ክልሎች ጭምር የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ  ለመከላከል ከክልሎቹ ጋር መረጃ በመለዋወጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም