ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት የልህቀት ማዕከል ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 05/2013 (ኢዜአ) የጋዜጠኞችን ሙያዊ አቅም ለማሳደግ የልህቀት ማዕከል እንደሚገነባ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ። የማዕከሉን ግንባታ ከሶስት ዓመት እስከ ሶስት ዓመት ከግማሽ ባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ ታቅዷል።

በኢትዮጵያ 13 ዩኒቨርሲቲዎች የጋዜጠኝነት ትምህርት እንደሚሰጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዷለም የዩኒቨርሲቲዎቹ የጋዜጠኝነት ስርዓተ ትምህርት ተመሳሳይነት ያለውና አንዱ ከአንዱ እየገለበጠ እንደሚጠቀምበት ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲዎቹ የሚሰጡ የተግባር ትምህርት ደካማ መሆን፣ ለሥራው የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማት አለመሟላትና ትምህርቱ በብቁ ባለሙያዎች ባለመሰጠቱ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች የሙያ ክህሎት ችግር ያጋጥማቸዋል ብለዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች የሚያጋጥማቸውን የአቅም ክፍተት ለመሙላት የሚረዳ የጋዜጠኝነት የልህቀት ማዕከል እንደሚገነባም አመልክተዋል።

ማዕከሉ ምሩቃን በሥራ ላይ ሆነው ሙያዊ አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት ድጋፍ እንደሚያገኙበት አቶ ወንድወሰን አስረድተዋል።

ባለስልጣኑ ማዕከሉ የሚቋቋምበት ትልመ ሀሳብ(ፕሮፖዛል) ከኳታር መንግሥትና ከአልጄዚራ ብሮድካስት ማሰራጫ ጋር ባለፈው ዓመት ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በትልመ ሀሳቡ ተጨማሪ ጉዳዮች ተካተው ዳግም ተዘጋጅቶ መላኩንም አስታውቀዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱንና ሥራዎች በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይሄዱ ተጽዕኖ ማድረሱን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰው፤ ለማዕከሉ የሚያስፈልግ ቦታ በመለየት ላይ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ለማዕከሉ ግንባታ የሚያስፈልገው በጀት በኢትዮጵያና በኳታር መንግሥታት እንደሚሸፈንና ግንባታው ከሶስት ዓመት እስከ ሶስት ዓመት ከግማሽ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልጸዋል።

የማዕከሉ የብሮድካስትና የሕትመት መገናኛ ብዙኃን የሚያስፈልጉት መሰረተ ልማት እንደሚኖሩትና የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ሙያዊ ስልጠና ይሰጥበታል ብለዋል አቶ ወንድወሰን።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም