ቀጥታ፡

ለክልሉ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው-የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት

ባህርዳር፤ ጥቅምት 04/2013 (ኢዜአ) ለአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምና ጸጥታ መረጋገጥ እንቅፋት የሚሆኑ ክስተቶችን በመመከት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ በ2013 ዓ.ም እና በ10 ዓመቱ ስትራተጂክ እቅድ ላይ ያተኮረ የጸጥታ ሃይሉን ቅንጅታዊ አሰራር ለማዳበር የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና በፍኖተ ሰላም ከተማ እያካሄደ ነው።

በቢሮ ሃላፊ ደረጃ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መኳንንት መልካሙ እንዳሉት በክልሉ ቀደም ሲል በተለያዩ ጊዜያት ያጋጥሙ ከነበሩት የጸጥታ ችግሮች አንጻር አሁን የጎላ የችግር የለም።

"ህዝቡ ለሰላም ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነው" ያሉት ኃላፊው የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚሯሯጡና በክልሉና ከክልሉ ውጭ የሚገኙ አንዳንድ ኃይሎች በአካባቢው ትርምስ እንዲፈጠር እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስትም የውስጥ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ከህዝቡ፣ ከምሁራንና ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ከተለያዩ ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር ጭምር ተከታታይ ውይይት በማካሄድ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ እንደሚሰራ ገልጸዋል። 

"ከውጭም እንደ ህውሃትና ኦነግ ሸኔ ያሉ ጸረ-ሰላም ሃይሎች አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበትን የአማራ ክልልን በማተራመስ አገር የማፍረስ ድብቅና ግልጽ ዓላማቸውን ለማሳካት ግንባር ፈጥረው እየሰሩ ነው"ብለዋል።

የክልሉ የጸጥታ ሃይልም የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅና የክልሉን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ አሰራርን በማዳበር ላይ የተመሰረተ አቅም እየገነባ መሆኑን ሀላፊው አስረድተዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚሊሻ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጎሸ አምባሁን  በበኩላቸው ዞናቸው ከሱዳን ጋር የሚዋሰን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ የጸጥታ ችግሮች የሚስተዋሉበት ነው ብለዋል።

"ከዚህም ባለፈ ህውሃት ሰርጎ ገቦችን ወደ ዞኑ በማስገባት ለዘመናት ተጋብተውና ተዋልደው፣ በፍጹም አንድነት መንፈስ ይኖሩ የነበሩትን የቅማንትና የአማራ ማህበረሰቦች ለማጋጨት የሚሰራው ስራ ቀላል አይደለም"ብለዋል።

ይህንና ሌሎች የጸጥታ ችግሮችን ለመቅረፍም ከማዕከላዊ፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞኖች ጋር በመተባበር ሊያጋጥሙ የሚችሉ ግጭቶችን ቀድሞየማክሸፍ ስራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

"የሚሊሻ፣ መደበኛ ፖሊስ፣ ልዩ ሃይልና ሌሎች የጸጥታ አካላት ሰላም ፈላጊ ከሆነው ህዝብ ጋር በማቀናጀት አሁን ላይ የሚስተዋለውን ሰላም ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የስልጠናው ዋና ግብ ነው" ብለዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን የሚሊሻ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋ ምስጋኔ እንዳሉት ዞኑ ከአጎራባች የትግራይ ህዝብ ጋር እርስ በዕርስ ተግባብቶና ተዋዶ የሚኖር በመሆኑ ለጸጥታ ስራ ጉልህ ሚና አለው።

"ሆኖም ግን ትህነግ እያሰለጠነ ከሚያስገባው ልዩ ኃይል በተደጋጋሚ ትንኮሳ ይደረጋል" ያሉት አቶ ተስፋ ህዝቡና የጸጥታ ኃይሉ በጋራ እየተከላከለ ሰላሙም እንደሚያስጠብቅ ገልጸዋል።

"የትግራይ እና የአማራ ህዝብ እስከ መቼውም አንድ ስለሆነ በሱ ልክ ነው የኛ ዞንም እየተከላከለ ያለው" ብለዋል። 

ከሌላው አጎራባች ክልል አፋር ጋርም መልካም ግንኙነት እንዳለ ገልጸው አልፎ አልፎ ከግጦሽ መሬት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ግጭቶችም በየጊዜው በህዝቡ እየተፈቱ እንደሚሔዱም አስረድተዋል። 

"ምንም እንኳን የሚደርሱ ትንኮሳዎችና ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል የሚሊሻና የሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ዝግጁነት ቢኖርም ቅድሚያ ለሁለቱ ክልል ህዝቦች ሰላም ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው" ብለዋል።

ለአራት ቀናት በሚሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይም በክልልና ዞን የሚገኙ የሚሊሻ፣ የፖሊስ፣ የአድማ ብተና፣ የልዩ ሃይልና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም