ቀጥታ፡

ለውጡን ለማስቀጠል እናግዛለን የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ወጣቶች

ጭሮ ሀምሌ 8/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጀመሩት የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስቀጠል የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጉባ ቆሪቻና ሚኤሲ ወረዳዎች  ወጣቶች ተናገሩ፡፡ ወጣቶቹ ለኢዜአ እንደገለጹት ቀደም ሲል በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች የመልካም አስተዳደርና የስራ እድል እንደሚቻችላቸው  ጥያቄዎችን ይዘው  አደባባይ ሲወጡ ቆይተዋል። ከሚኤሶ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል   ወጣት ይትባረክ ለገሰ በሰጠው አስተያየት  አሁን የተገኙ የመደመርና የሰላም ለውጥ ፍሬዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተደጋግፎ መስራት እንዳለበት አመልክቷል። "ለውጡን ተከትሎ እየታዩ ያሉት  ውጤቶች በማንኛውም ኃይል ተደናቅፈው ወደኋላ እንዳይመለሱ ለማድረግ የድርሻዬን ለማበርከት ዝግጁ ነኝ" ብለሏል ። "ወጣቱ ከተገኘው ሰላምና ለውጥ ዋነኛ ተጠቃሚ መሆኑን በመረዳት  ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻውን ሊወጣ ይገባል" ያለው ደግሞ ሌላው  የወረዳው ነዋሪ ወጣት አብዲ ኢድሪስ ነው፡፡ በጉባ ቆሪቻ ወረዳ የከሞና ከተማ ነዋሪ  ወጣት ያዕቆብ ደመረው በበኩሉ ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው ሰላም ሲኖር በመሆኑ ወጣቱ ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚጠበቅበት ተናግሯል፡፡ ወጣቱ እንዳለው መንግስት በአሁኑ ወቅት እያደረጋቸው ያሉት የለውጥ እንቅስቃሴዎች በዘላቂነት ለማስቀጠል ሁሉም ወጣት መረባረብ አለበት፡፡ የከተማው ቀበሌ አንድ ነዋሪዋ ወጣት ሰርክአዲስ አጥናፌ  ልዩነቶችን በመነጋገርና በመወያየት መፍታት እንደሚገባ ጠቅሳ " ወጣቶች ችግሮችን በስሜት ከማራገብ ይልቅ በመነጋገርና በመወያየት የመፍታት ባህል ማደበር ይጠበቅብናል "ብላለች፡፡ ዶክተር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ ወዲህ  በርካታ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገባቸውን ያስተወሱት ወጣቶቹ  የጀመሩት የለውጥ እንቅስቃሴ አጠናክሮ ለማሰቀጠል የበኩላቸው እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የወጣቱን ተሳትፎ  በማሳደግ ረገድ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም