ቀጥታ፡

በፖላንድ በሚካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር የሚሳተፈው የልዑካን ቡድን ዛሬ ማምሻውን ወደ ስፍራው ያቀናል

አዲስ አበባ ጥቅምት 4/2013 (ኢዜአ) በፖላንድ ግደኒያ ከተማ በሚካሄደው የግማሽ ማራቶን የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማምሻውን ወደ ስፍራው ያቀናል። 

24ኛው ዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶን ውድድር ጥቅምት 7 ቀን 2013 ዓ.ም በፖላንድ ግደኒያ ከተማ ይካሄዳል።

አትሌቶች አሰልጣኞችና የቴክኒክ ባለሙያን ጨምሮ 15 አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን ዛሬ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ውድድሩ ወደሚካሄድበት ስፍራ እንደሚያቀና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የልዑካን ቡድኑ ትናንት ማምሻውን ለገጣፎ በሚገኘው የጥሩነሽ ዲባባ ሆቴል አሸኛኘት እንደተደረገለት ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በውድድሩ በወንዶችና በሴቶች በተመሳሳይ በአምስት አምስት አትሌቶች እንደምትወከል ገልጿል።

አትሌቶቹ የተመረጡት በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደ የሰዓት ሟሟያ ውድድር እንደሆነና በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች በተመሳሳይ 10 አትሌቶች ተሳትፈዋል።

የሰዓት ሟሟያ ውድድር የተሳተፉ አትሌቶች የተመረጡት በቢሾፍቱ ባለፈው ዓመት በተካሄደው 13ኛው የኢትዮጵያ የግማሽ ማራቶን ውድድርና በውጭ አገር በተካሄዱ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ያላቸውና ወረርሽኙ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ያላቸውን አቅም መሰረት በማድረግ እንደሆነ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከአንድ እስከ አምስት የወጡ ተወዳዳሪዎች በፖላንዱ ዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶን ውድድር እንዲሳተፉ መመረጣቸውንም አመልክቷል።

በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ላለፉት ሶስት ሳምንታት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መመሪያን በተከተለ መልኩ ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸው ተገልጿል።

ሁሉም የአትሌቲክስ ልዑካን ቡድኑ አባላት ከትናንት በስቲያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን መረጋገጡንና የተደረገው ምርመራ የፖላንድ መንግስትና የዓለም አትሌቲክስ ባስቀመጡት መመሪያ አማካኝነት የተከናወነ መሆኑን ነው አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ያስታወቀው።

የዓለም አትሌቲክስ የፖላንዱ ውድድር መጋቢት ወር 2012 ዓ.ም እንዲካሄድ ቀን ቆርጦለት የነበረ ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሩን ማራዘሙ ይታወሳል።

በ24ኛው ዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶን ውድድር ከ62 አገራት የተወጣጡ ወንድ 157 ሴት 126 በድምሩ 283 አትሌቶች እንደሚሳተፉ የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል።

እ.አ.አ 2018 በስፔን ቫሌንሺያ ከተማ በተካሄደው 23ኛው ዓለም አቀፍ የግማሽ ማራቶን ውድድር በሴቶች አትሌት ነጻነት ጉደታ በወንዶች ኬንያዊ አትሌት ጂኦፍሬይ ካምዎሮር አሸናፊ መሆናው የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም የግማሽ ማራቶን ውድድር ታሪክ በሴቶች ሶስት የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን አትሌት ነጻነት ጉደታ፣አትሌት ብርሃኔ አደሬና አትሌት መሰረት ሃይሉ ሜዳሊያዎቹን አስገኝተዋል።

በዓለም የግማሽ ማራቶን ውድድር በወንዶች ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው አንድ ጊዜ ሲሆን እሱም አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ እ.አ.አ በ2001 በእንግሊዝ ብሪስቶል ከተማ በተካሄደው ውድድር አሸናፊ የሆነበት ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም የግማሽ ማራቶን ውድድር ታሪክ በግልና በቡድን 11 የወርቅ፣16 የብር፣17 የነሐስ በድምሩ 44 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም